ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ፈተናዎች እንድትሻገር ሁሉም በየቤተ እምነቱ ፀሎትና ምህላውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

ሚያዚያ 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ፈተናዎች እንድትሻገር ሁሉም በየቤተ እምነቱ ፀሎትና ምህላውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪነት ተዘጋጅቶ ከሚያዚያ 7 ቀን 2013 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው አገራዊ የፀሎትና ምህላ መርሀ ግብር ዛሬ ተጠናቋል።

በጸሎትና ምህላ መዝጊያ ፕሮግራም የተለያዩ ቤተእምነቶች አባቶች፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አገራዊ ሁኔታውን በማጤን ያዘጋጀው አገር አቀፍ የፀሎትና ምህላ በተቀመጠለት ጊዜ በስኬት መጠናቀቁ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እምነቶች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ሲፈተኑ ተፈትነው፣ በፖለቲካ ተቃርኖ ሲደሙ ደምተው ዛሬ ላይ መድረሳቸው ተነግሯል።

አገሪቷን ማጥፋት የሚፈልጉ ጠላቶች ሲንቀሳቀሱ መጀመሪያ የሀይማኖት ተቋማትን ኢላማ ማደረጋቸውም ተጠቁሟል።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም ቤተ እምነቶች የአገር ሠላምና አንድነት ወካይ ማንነት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩና አሁንም እያገለገሉ ያሉ ስለመሆናቸውም ነው የተገለጸው።

ከዚህ አገራዊ ሚናቸው በመነሳት ለቆሙለትና ለሚከተሏቸው ምዕመናን የእረኝነት ሀላፊነት እንዲሁም የተሰጣቸውን ሠማያዊ ተልዕኮ እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በፀሎትና ምህላ መርሃ ግብሩ አገራዊ ጥሪውን የተቀበሉ ከ14 በላይ ሚዲያዎች ዓላማው እንዲሳካ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበርም ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ተወካይ ብጹዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ፈተናዎች እንድትሻገር ፀሎትና ምህላው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

አገራዊ የፀሎትና ምህላ መርሀ ግብሩ ዛሬ ቢጠናቀቅም ሁሉም ምዕመን በየቤቱ ለአገር ሠላምና አንድነት ተግቶ ፈጣሪውን በፀሎትና ምህላ እንዲጠይቅም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፈቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ተወካይ ሼህ መሀመድ ኢድሪስም የአገሪቷ ልጆች ተከባብረውና ተዋደው የሚኖሩባት አገር እንድትሆን ፀሎትና ምህላው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌልም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የዜጎችን ህይወት እያሳጣ መሆኑን፣ በግጭቶችም ሞትና መፈናቀል ማጋጠሙን ተናግረዋል።

እነዚህን ችግሮች ሊያስቆም የሚችል ፈጣሪ ብቻ በመሆኑ አገራዊ የፀሎትና ምህላ መርሀግብሩ ዛሬ ቢጠናቀቀም ፀሎትና ምህላው ሳይቋረጥ ሁሉም በቤቱ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

መተባበር ለበጎ ነገር እንጂ ለጥፋትና ለደም መፋሰስ አይገባም ያሉት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ለኢትዮጵያ መጻኢ እድል የሚሰሩ ወገኖች የሰላም መሳሪያ በመሆን ልዩነቶችን ወደ ጠረጴዛ እንዲያመጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት እንዲመጣና አንዳችን ለሌላችን አለኝታና መከታ ነን የሚል አስተሳሰብ እንዲፈጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የተጀመረው ፀሎትና ምህላ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

በመዝጊያ መርሀግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው አገሪቷ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ የፈተና ወቅትም በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች፣ መፈናቀሎች እንዲሁም ሞቶች እየተደመጡ፤ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ በርካቶች እየሞቱ መሆኑን አመላክተዋል።

የተደረገው ፀሎትና ምህላ በዚህ እንደማይበቃና ለሰላም ለአንድነት እንዲሁም ከፈተና ለመውጣተ ፀሎቱ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

ካለንበት ሁኔታ ወጥተን የሁላችንም የሆነችውን ኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ ቦታ እንድትደርስ በጋራ እንቁም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም