ቀጥታ፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ ገበያን መሰረት ያደረገ የተማሪዎች ቅበላ እንደሚኖር ተገለፀ

ሚያዚያ 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመጀመሪያ ዲግሪ በሚሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞች ከአቅርቦትና ገበያ አንፃር ያለባቸውን ችግር የሚዳስስ የስራ ገበያ ሁኔታ ጥናት እንደሚደረግ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዚሁ መሰረት በ2014 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ ገበያን መሰረት ያደረገ የተማሪዎች ቅበላ ይደረጋል ነው ያለው ሚኒስቴሩ።

የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት የምስረታ ጉባዔ ዛሬው ተካሂዷል።

ምክር ቤቱ ከ200 በላይ የሙያ ማህበራትን ያካተተ ሲሆን በትምህርት ጥራትና አግባብነት ላይ አተኩሮ ይሰራል ነው የተባለው።

በምስረታ ጉባዔው በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፣ የተለያዩ የሙያ ማህበራት አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

ፕሮፌሰር ሂሩት ትምህርት የሰው ሀብት ልማት ማዕከል መሆኑንና የአንድ አገር እድገት፣ ልማትና ብልፅግናን የሚወሰን እንደሆነ ተናግረዋል።

ጥራት ያለው ትምህርት ሚዛናዊ፣ አስተዋይና በቴክኖሎጂና በፈጠራ የተሞሉና ቀና ልቦና ያላቸው ገራም ዜጎች እንዲኖሩ ያስችላል ነው ያሉት።

የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት ውጤታማ ስራዎች ቢከናወኑም የጥራት ችግር እንዲስተዋልም አንስተዋል።

የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ መንግስት በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሲሰራ መቆየቱንም ገልፀዋል።

የምክር ቤቱ መመስረት ለትምህርት ጥራትና አግባብነት ጉልህ አስተዋፅኦ ያለው ከመሆኑ ባለፈ ከስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ጀምሮ ተማሪዎችን ለማብቃት በጋራ መስራት እንደሚያስችል አብራርተዋል።

ምክር ቤቱ በገለልተኝነት የሚሰራ ቢሆንም የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ ከሚኒስቴሩ ጋር ተባብሮ እንደሚሰራም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ የምሩቃን ምዘና፣ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያና የዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ሲመዘን ሚናውን የሚወጣ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከምክር ቤቱ ጋር በመተባበር በመጀመሪያ ዲግሪ በሚሰጡ 211 የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች ከአቅርቦትና ገበያ ጋር ያላቸውን ችግር ለመዳሰስ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በቅድመ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች የስራ ገበያ ሁኔታ ጥናት መሰረት በቀጣዩ የ2014 የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቅበላ የሚከናወን መሆኑንም አስረድተዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴ እንዳሉትም በምክር ቤቱ የተካተቱ የሙያ ማህበራት የትምህርት ጥራትና አግባብነት ለማረጋገጥ የሚረዱ ናቸው ብለዋል፡፡

በቀጣይ ለተቋማት እውቅናና እድሳት በሚሰጥበት ጊዜ ኃላፊነት እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም