ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በህዳሴው ግድብ ላይ ጥናቶችን በማካሄድ እውነታውን ለዓለም ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል-ሚኒስቴሩ

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 15 / 2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በህዳሴው ግድብ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንዲሁም ስነ-ምህዳራዊ ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን በማድረግ የግድቡን እውነታ ለዓለም ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

" የምሁራን ትብብርና ተሳትፎ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዘላቄታዊ ጠቀሜታ " በሚል መሪ ሃሳብ አራተኛው ሃገር አቀፍ የትምህርት ተቋማት ፎረም ዛሬ በአሶሳ  ተጀምሯል፡፡

በፎረሙ ላይ የተገኙት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፤ የህዳሴ ግድብ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማምጣት ተቃርቧል፡፡

ይህም ከድህነት ወደ እድገት የሚያሸጋረን  ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ግድቡ አስመልክቶ የብሔራዊ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤትን ጨምሮ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የምሁራንን የውይይት መድረክ በማዘጋጀት የመረጃ ተደራሽነት ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከግድቡ ጋር የሚገናኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ምህዳራዊ ጉዳዮች ጥናታዊ ምርምሮችን በማካሄድ እና ለችግሮች መፍትሔ ማፍለቅ እንደሚጠብባቸው ገልጸዋል፡፡

እውነታውንም ለዓለም ማህበረሰብ ተደራሸ ማድረግ እንዳለባቸው ፕሮፌሰር አፈወርቅ አስገንዝበዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ግንባታ ወደ 80 በመቶ መድረሱን የገለጹት  ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር  ዶክተር አረጋዊ   በርሄ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን በቁጭት ተነሳስተው ለጀመሩት የህዳሴ ግድብ እስካሁን 15 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡

ግድቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሃገራዊ መግባባትን እንዲጠናከር ማድረጉን ዶክተር አረጋዊ  በርሄ አስታውቀዋል፡፡

ግድቡ አሁን የሚፈጸምበትን የትኛውንም ሴራ አልፎ ለአገልግሎት እንደሚበቃ እምነታቸው መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ 86 በመቶ የአባይ ወንዝ ውሃ አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ ለወንዙ ምንም አስተዋጽኦ ያላደረጉ ግብጽ እና ሱዳን በበላይት ለዘመናት መጠቀማቸውን አስታውሰው፡ ይህም ፍትሃዊነት የጎደለው ነው ብለዋል፡፡

በወንዙ አጠቃቀም ላይ ያለውን ኢ-ፍትሐዊነት መሟገት እና ጉዳዩንም ለዓለም ማህበረሰብ በሚገባ ማስገንዘብ የምሁራን ተቀዳሚ ሃላፊነት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ባበክር ከሊፋ የህዳሴው ግድብ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለምናደርገው ሽግግር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ግንባታው እንስኪጠናቀቅ የክልሉ መንግስት እና ህዝብ የአካባቢ ጥበቃ ስራን እንዲሁም ጸጥታውን አስተማኝ ለማድረግ ከመቼውም በላይ እንደሚጥሩ አመልክተዋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን ተጠቅማ እንዳትለማ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጫና እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሶስትዮሽ የድርድር ሰበብ የሚደርስባትን መቋጫ የሌለው ትንኮሳ መኖሩን ዶክተር ከማል ጠቅሰዋል፡፡

በአባይ ወንዝ ላይ ፍሃዊነት የጎደለው የግብጽ የዘመናት የበላይነት መሰበር ይኖርብታልም ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች በአባይ ጉዳይ ወራት እየጠበቅን መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን በምርምር ስራዎቻችን ጉዳዩን አካተን መስራት የግድ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እስከ ነገ በሚቀጥለው ፎረሙ በሀገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምህራን እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም