ቀጥታ፡

የፌደራሊዝም ስርዓት ጽንሰ ሃሳብና አተገባበር ግንዛቤ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ ፣ሚያዚያ 15/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓተ መንግስት ጽንሰ ሃሳብና አተገባበር ላይ የሚስተዋሉ ብዥታዎች በማጥራት በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም የግንዛቤ ማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የሠላም ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትሩ በሲዳማ ክልል ለሚገኙ የሠላምና ጸጥታ ሴክተር የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በፌደራሊዝምና የህግ የበላይነት ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጫ ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

በሠላም ሚኒስቴር የፌደራሊዝምና የመንግስታት ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብዙነህ ምክሩ በመድረኩ እንዳሉት በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓት ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም ጽንሰ ሃሳብና አተገባበር ላይ ብዥታ መኖሩን በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል።

የፌዴራል ስርዓቱ ሃገር በታኝ፣ ኢህአዴግ አመጣሽና በኢትዮጵያ ብቻ እየተተገበረ የሚገኝ ተደርጎ በብዙ ዜጎች ዘንድ እየተወሰደ መሆኑን በጥናቱ እንደተመላከተ ጠቅሰዋል።

ይህም የሆነው የማስረጽ ስራ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ባለመሰራቱ ነው ብለዋል።

የፌደራል ስርዓት ብሄሮች በፈቃዳቸው ሃገራዊ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ እድል የሚሰጥና ልማትን ለማምጣት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ችግሩን ለማቃለል ግንዛቤ የማሳደጉ ስራ እስከ ማህበረሰቡ የሚዘልቅ ውይይት ለማካሄድ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የሲዳማ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አማኑኤል መንግስቱ በበኩላቸው፤ የበርካታ ብዝሀነት ባለቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ ጠንካራ የፌደራሊዝም ስርዓት መከተል ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

በተለይም ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም ስርዓት ብዝሃነቶችን ለማስተናገድና ዴሞክራሲን ለማጎልበት ያለውን ፋይዳ በአግባቡ በመገንዘብ ስርዓቱን ከአሃዳዊ አቀንቃኞች ለመታደግ መርሆችን ጠንቅቆ ማወቅን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንዱ አካል ነው ፤ ምርጫው ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሠላምና ጸጥታ ሴክተር ያለበትን ድርብ ሃላፊነት መወጣት አለበት ብለዋል።

በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የሃዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ የሠላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደጀኔ ጃጎ የፌደራሊዝም ስርዓት ምንነትና ባህሪያት ላይ የነበራቸውን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

ከመድረኩ የሚያገኙትን ግንዛቤ በክፍለ ከተማው ለሚገኙ አመራሮችና የማህበረሰብ ክፍሎች ለማካፈል እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ የፌደራሊዝም መሠረታዊ ሀሳብ፣ የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ዋና ዋና ገጽታዎች፣ ሰብአዊ መብቶች፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ውይይት ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም