ቀጥታ፡

በመዲናዋ ከሚገኙ የአገር ውስጥ የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች 43ቱ ፈቃድ የላቸውም

አዲስአበባ፣ ሚያዚያ 15/2013(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከሚገኙ የአገር ውስጥ የግል ስራና ሠራተኞች አገናኝ ኤጀንሲዎች 122ቱ በፈቃድ የሚሰሩ ሲሆኑ 43ቱ ፍቃድ እንደሌላቸው የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አሰሪና ሠራተኛ ኮንፌዴሬሽኖች የግል ስራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ የተደረገውን ጥናት አስመልክተው የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

አንዳንድ ኤጀንሲዎች ከተሰጣቸው ፈቃድና ዓላማ ውጭ በሌሎች ህገ-ወጥና እኩይ ተግባራት ተሰማርተው መገኘታቸው ለጥናቱ መነሻ መሆኑ ተገልጿል።

የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ወይንም የስራ ፍቃድ ሳይኖራቸው የንግድ ፍቃድ በማውጣት ብቻ በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ኤጀንሲዎች መኖራቸውም ተመላክቷል።

የጥናቱ ዓላማ በዘርፉ የተሰማሩ ኤጀንሲዎች ምን ያህል ሕግን ተከትለው እየሰሩ መሆኑን ለመፈተሽና በሕገ ወጥ ተግባር የተሰማሩትም ለሕግ የሚቀርቡበትን የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ መሆኑ ተገልጿል።

ጥናቱ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 313 ኤጀንሲዎች ላይ እንደተደረገም ተጠቁሟል።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት የአገር ውስጥ ኤጀንሲዎች የሚተዳደሩበት ደንብ ላይ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።

የመነሻ ደመወዝ ወለል፣ የሙያ ደህንነትና የወሊድ ፈቃድ ማሻሻያ ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ጠቅሰዋል።

ነገር ግን አንዳንድ በአገር ውስጥ የግል ስራና ሠራተኞችን የሚያገናኙ ኤጀንሲዎች ሕግን ተከትለው እንደማይሰሩ ገልጸው እነዚህም በጥናት ተለይተዋል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ 157 ኤጀንሲዎች በትክክለኛ አድራሻቸው የተገኙ ሲሆኑ 71 የሚሆኑት ደግሞ አድራሻ እንደሌላቸው በጥናቱ ታይቷል።

በኤጀንሲዎቹ በአካል በመገኘት በተደረገ ማጣራትም 122 የሚሆኑት ፈቃድ እንዳላቸው፤ 43 ደግሞ ፍቃድ እንደሌላቸው እንደተደረሰበት ጠቁመዋል።

በጥናቱ ከተሸፈኑ 157 የግል የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች መካከልም 11 የሚሆኑት ኃላፊነት ወስደው በሚጠብቁት ተቋም ላይ ስርቆት እንደተፈጸመ ጥናቱ አመላክቷል ብለዋል።

የጥናቱን ውጤት መሰረት በማድረግ በህገ ወጥ መንገድ ሲሰሩ የተገኙና ሊገኙ ያልቻሉ ኤጀንሲዎች በዘርፉ መቀጠል የለባቸውም የሚል የውሳኔ ሀሳብ መተላለፉን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

በጥቅሉ 144 ኤጀንሲዎች ከሚመለከታቸው አካላት የወሰዷቸውን የብቃት ማረጋገጫ፣ የስራ ፈቃድና የንግድ ፍቃድ በመመለስ ከዘርፉ እንዲወጡ የውሳኔ ሀሳብ መቅረቡንም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ አድራሻቸው ያልተገኘ 71 ኤጀንሲዎች ላይ ክትትል በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው መንግስት የሠራተኞችን ችግር ለማቃለል በዚህ መልክ ጥናት ማድረጉ አበረታች ተግባር ነው ብለውታል።

በጥናቱ የተለዩ ችግሮችን ለመፍታትና በቀረቡ ምክረ ሀሳቦች አፈጻጸም ላይ በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመርም ኤጀንሲዎች ሕግና ደንብ አክብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አቶ ታደለ ሕግና ደንብ አክብረው ለሚሰሩ ኤጀንሲዎች እውቅና እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም