ቀጥታ፡

የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ላሉ 10 የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች የማሰራጫ መሳሪያ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 15/2013(ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ላሉ 10 የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች 76 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ የማሰራጫ መሳሪያ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፋ ለ10 የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎች የተሰጠ ሲሆን እገዛው ወቅታዊና ትኩስ መረጃ በአግባቡ ለማድረስ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ተብሏል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እድሪስ፣ የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎቹ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰጡትን አገልግሎት ቀጣይነት ለማረጋገጥ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎች በመረጃ የበለጸገ ዜጋ ለማፍራት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ እነዚህን የማህበረሰብ ራዲዮ ለማጠናከር የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ መሃመድ አረጋግጠዋል።

በቀጣይም የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ የልማት ፕሮግራም ምክትል ተወካይ አቶ ክሊዮፓስ ቶሮሪ፤ በኢትዮጵያ ላሉ 10 የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች 76 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የሚያወጡ የማሰራጫ መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ድርጅቱ የመገናኛ ብዙሃንና የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎችን አቅም ለመገንባት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎች ከሌሎች የመገናኛ ብዙሃን በተለየ መልኩ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን በማይደርሱባቸው አካባቢዎች የተሻለ መረጃ በመስጠት ትልቅ ሚና ስላላቸው ይህንኑ ጥረት ለመደገፍ መቻሉ ለድርጅቱ ትልቅ እርካታ መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጅቱ በአገሪቱ የሚከናወኑ የለውጥ ስራዎችን እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ ሲደረጉ የነበሩ ማሻሻያዎችን ሲደግፍ እንደነበር አስታውሰው በቀጣይ የመረጃ ተደራሽነቱን ለማስፋት ድጋፋ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በዛሬው እለት ድጋፍ ከተደረገላቸው የማህበረሰብ ራዲዮ  ጣቢያዎች  መካካከል  ሱዴ ፤ አርጎባ ፤ፍኖተ ሰላም ፤ ሰቆጣና ከፋ ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም