ቀጥታ፡

በክልሎች መካከል ፍትሃዊ የሀብት አጠቃቀም ማስፈን የሚያስችል የድጎማ በጀት ቀመር ተግባራዊ ይሆናል - የፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15/2013(ኢዜአ) በሁሉም ክልሎች የተመጣጠነ እድገት በመፍጠር ፍትሃዊ የሀብት አጠቃቀም ማስፈን የሚያስችል በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት ቀመር ተግባራዊ እንደሚሆን የፌደሬሽን ምክር ቤት ገለጸ፡፡

በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት ቀመር እስካሁን ሲሰራበት በነበረው ጥቅል የድጎማ በጀት ማዳረስ ያልተቻለውን የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነት ክፍተት በመሙላት ወደኋላ የቀሩትን ወደ ፊት ማምጣት ያስችላልም ተብሏል፡፡

የፌዴሬሽን ምክትር ቤት በጥቅል ዓላማ የድጎማ በጀት፣ የፌዴራል መንግስት የመሰረተ ልማት ስርጭት ፍትሃዊነት የድጋፍና ክትትል ስርዓት ዙሪያ ያስጠናውን ጥናት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በተገኙበት አቅርቧል፡፡

በዚሁ ጊዜም ከክልል ወደ ወረዳዎች የሚደረገውን የፊስካል ሽግግር ስርዓት ጥናት ለማካሄድ የተዘጋጀ የጥናት መነሻ ሀሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ እንደተናገሩት እስካሁን በነበረው ሂደት ሲሰራበት የነበረው ጥቅል ዓላማ ያለው የድጎማ በጀት ቀመር ብቻ ነበር፡፡

በዚህም በክልሎች መካከል የተመጣጠነ እድገት ለማምጣትና በልማት ወደኋላ የቀሩ ክልሎችን በግልጽ አሰራር መደገፍ አልተቻለም ብለዋል፡፡

በመሆኑም በሁሉም ክልሎች ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት ለማስፈንና የተመጣጠነ እድገት ለማምጣት በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት ቀመር በአሰራር ማበጀት አስፈልጓል ብለዋል።

በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት በተለያዩ ተቋማት በዘፈቀደ ሲሰራበት እንደነበር ያስታወሱት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ይህ ልቅ የሆነ አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት መንገድ እንዲከናወን መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት አሰራር ስርዓት ወጥ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ጥቅል ዓላማ ባለው የድጎማ በጀት ብቻ ተወስኖ የነበረውን የክልሎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አገራዊ እድገት እንዲመዘገብ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት መካነ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ጌትነት አለሙ ክልሎች ገቢ የመሰብሰብ መብታቸው ዝቅተኛ፤ ወጪያቸው ደግሞ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ብቻ በተወሰደ መረጃ ክልሎች ያመነጩት ገቢ 41 በመቶ ሲሆን ቀሪው 59 በመቶ የተሸፈነው በፌዴራል መንግስት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት ጥቅል በድጎማ በጀት ያልተሸፈኑ ክፍተቶችን በመሙላት የክልሎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ልማት ያሳድጋል ብለዋል፡፡

የክልሎች የድጎማ በጀት ከአገራዊው ጥቅል ገቢ ምን ያህል እንደሆነ በመቶኛ በግልጽ የተቀመጠ ባለመሆኑ መስተካከል አለበትም ተብሏል፡፡   

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሃይሉ ኤልያስ፤ በክልሎች መካከል ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና እድገት እንዲኖር የሚመለከታቸው አካላት ተናበው መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡

በተለይም በቀጥታ የሚመለከታቸው የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶችና ተቋማት በሕገ መንግስቱና በአዋጅ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት ሃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት የተጠያቂነት ስርዓት ለማስፈን ስራዎች መቼ፣ እንዴትና ለምን እንደሚሰሩና እንደሚጠናቀቁ ማወቅ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም