በኢትዮጵያ ደካማና ታዛዥ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የተዘረጉ የውጭ ስውር እጆችን መጠንቀቅ ይገባል - አቶ ኤልያስ ወንድሙ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ደካማና ታዛዥ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የተዘረጉ የውጭ ስውር እጆችን መጠንቀቅ ይገባል - አቶ ኤልያስ ወንድሙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15/2013/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ደካማና ታዛዥ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የተዘረጉ የውጭ ስውር እጆችን መጠንቀቅ ይገባል ሲሉ የፀሃይ አሳታሚ ድርጅት ባለቤት አቶ ኤሊያስ ወንድሙ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም መጪውን ምርጫ አስመልክቶ ከክልል ርዕሳነ መስተዳደሮችና ከከተማ መስተዳደር ከንቲባዎች ጋር ባደረጉት ውይይት "በኢትዮጵያ ደካማ መንግስት ለማቆም የሚሰሩ የውጭ አካላት አሉ" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
አቶ ኤልያስ በአሜሪካ የሚገኘው የፀሃይ አሳታሚ ድርጅት መሥራችና ባለቤት እንዲሁም የዓለም አቀፉ የስትራቴጂክ ጥናት ማኅበር አባል ናቸው።
የዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ጥናት መጽሄት መሥራችና አርታኢ ሲሆኑ፤ በአሜሪካ ሎስአንጀለስ የመጽሃፍ ግምገማ ላይም በአርታኢነት ይሳተፋሉ።
ኢዜአ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጣልቃ ገብነት አስመልክቶ ከአቶ ኤሊያስ ጋር ቆይታ አድርጓል።
በርካታ የውጭ አካላት የተበታተነችና አንድነቷ ያልተጠበቀ ኢትዮጵያን በመፍጠርና ታዛዥ መንግስት በማቆም በቀጠናው የፈለጉትን ተግባር መፈጸም እንደሚሹ ነው የተናገሩት።
አሁን የሚታዩ የግጭት አጀንዳዎች የእኛ ሳይሆኑ ከጀርባ በማይታይ ስውር እጅ የተሸረቡ ናቸው ሲሉ ይገልጻሉ።
በመሆኑም እንደ ሕዝብ ይህን ተገንዝበን ለመፍትሄው መስራት ካልቻልን ከጥፋቱ የሚያመልጥ አካል አይኖርም ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድም ከክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ጋር ሲወያዩ እነዚህ አካላት ምርጫውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያን በማመስ "የደካሞች ስብስብ ያለው መንግስት ለመፍጠር እየጣሩ ነው" ብለዋል።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እኩይ ሀሳባቸውን የገዙ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር በር የሚከፍት አካሄድ እየተከተሉ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ኤልያስ የአድዋን ድል ሽንፈት መቀበል ያቃታቸው የውጭ ኃይሎች ከድሉ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያን የማዳከምና የማተራመስ ሴራ ላይ እንዳሉ በመግለጽ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ አጠናክረዋል።
ድሉ እንደ ተራራ ራሳቸውን በከፍታ አስቀምጠው የነበሩ ወራሪዎች መሸነፍ እንደሚችሉ ያመላከተ መሆኑ ደግሞ "ጥርስ የነከሱ የዕድሜ ልክ ጠላት ፈጥሮብናል" ነው ያሉት።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ እነዚህ አካላት ሴራቸውን ለመፈጸም ሾልከው የሚገቡበትን ቀዳዳ ለማበጀት ጊዜ ወስደው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ሲያጠኑ ቆይተዋል።
እንደ አድዋ ድል ሁሉ ጠንካራ ኢትዮጵያ መኖሯ ጥቅማቸውን የሚነካባቸው ኃይሎች ዛሬም በስፋት ስውር እጃቸውን አስገብተው ኢትዮጵያን ለማተራመስ እየሰሩ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በተለይ ምሁራን ጥናትን መሰረት በማድረግ መንግስትን ማማከርና አቅጣጫ ማሳየት አለባቸው ይላሉ።
ኢትዮጵያዊያን ማናቸውንም አይነት ቁርሾዎች በይቅርታ በማለፍ ለጠላት ሴራ በር መዝጋት እንዳለባቸውም አቶ ኤልያስ ጠቁመዋል።