ቀጥታ፡

በጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ማሻሻያ መረሃ ግብር ይፋ ተደረገ

ጋምቤላ ፤ ሚያዚያ 15/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል የተሟላ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የጤና ማሻሻያ /አይ ኬር ኢኒሼቲቭ /መረሃ ግብር ይፋ ተደረገ።

"አይ ኬር ኢኒሼቲቭ " በሃገር አቀፍ ደረጃ በ24 ሆስፒታሎች የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል፣ ሩህሩህ ፣ተገልጋይ አክባሪና ተንከባካቢ የጤና አገልግሎት ስርዓትን ለመገንባት ታሳቢ አድርጎ የተጀመረ መሆኑ ተመልክቷል።

መረሃ ግብሩ በጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል ትናንት ይፋ ሲደረግ የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኡሞድ ጆን እንዳስረዱት፤ ሆስፒታሉ በክልሉ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ጨምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ እያስተናገደ ይገኛል።

ሆኖም ሆስፒታሉ ባለበት የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች ጥበት፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ የሰው ኃይል፣ የመድኃኒትና ሌሎች ችግሮች ምክንያት የሚፈለገውን የህክምና አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ መረሃ ግብሩን ለመተግበር በተደረገው ጥናት ችግሮቹን በመለየት የመፍቻ እቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመው ለእቅዱ ማስፈፀሚያም ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

መረሃ ግብሩ ይፋ ሲደረግ በስፍራው የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለምፀሃይ ጳውሎስ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር ጋምቤላን ጨምሮ በ24 ሆስፒታሎች የጤና አገልግሎት ማሻሻያ መረሃ ግብር /አይ ኬር ኢኒሼቲቭ/ መጀመሩን ገልጸዋል።

በሆስፒታሎች የተጀመረው መረሃ ግብር የህክምና አገልግሎቱን በማዘመን ለሌሎች መሰል ተቋማት ማስተማሪያ ሊሆኑ በሚችሉ መልኩ ለማብቃት ያሉባቸው ችግሮች ተለይተው ለመፍታት ባለድርሻ አካላትን ባካተተ መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በጋምቤላ ሆስፒታል ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ በእራስ አቅም ሊፈቱ የሚችሉትን ለማድረግ ደግሞ የሆስፒታሉም ሆነ የክልሉ አመራር ጠንክሮ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሩድ ጋሪዊች እንዳሉት፤ የጋምቤላን ብቻ ሳይሆን ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ሆስፒታሎችን አገልግሎት ለማሻሻል እቅድ አውጥተው እየሰሩ ነው።

ይሁን እንጂ በጋምቤላ ጠቅላላ ሆስፒታል የተቀየሰውን መረሃ ግብር ሆነ በሌሎቹ ሆስፒታሎች የህክምና አገልግሎቱን ለማሻሻል የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን አስታውቀዋል።

በጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል ያሉትን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንደሚሰራ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኡቦንግ ኡቶው ናቸው።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የፌዴራልና ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ሆስፒታሉን መጎብኘታቸው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም