የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ለተጫወቱት ገንቢ ሚና በተመድ የኢፌድሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት አድናቆቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ለተጫወቱት ገንቢ ሚና በተመድ የኢፌድሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት አድናቆቱን ገለጸ
ሚያዚያ 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ወዳጅ በመሆን ለተጫወቱት ገንቢ ሚና፣ ለሰጡት ድጋፍና ለነበራቸው ግንዛቤ በተመድ የኢፌድሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት አድናቆቱን ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት እና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የፕሬስ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫው በተመድ የኢፌድሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በሚመለከት ያወጣውን የፕሬስ መግለጫ መመልከቱን ገልጾ፤ወዳጅ ለሆኑ የም/ቤቱ አባላት ሁሉ ለተጫወቱት ገንቢ ሚና፣ ለሰጡት ድጋፍና ለነበራቸው ግንዛቤ ያለውን አድናቆት ገልጿል።
በትግራይ ክልል የተካሄደው ህግና ሥርአትን የማስከበር ተግባር የሀገር ልአላዊነትን በሚያስከብር ህጋዊ ማዕቀፍ መሰረት የተከናወነ መሆኑን ጽ/ቤቱ እንደሚያምን አስታውቋል።
በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተፈላጊውን ድጋፍ በማቅረብ ላይ ሲሆን በቀጣይነትም ከፍ ያለ ሀብት በማሰባሰብ ድጋፍን የሚያቀርብ ይሆናል ብሏል መግለጫው።
በዚህ አጋጣሚ አለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች በትግራይ ክልልና በሌሎች ቦታዎች ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት ለማሟላት ድጋፋቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪያችንን እናቀርባለንም ነው የተባለው።
በሰብአዊ መብት ጥሰትና በፃታዊ ጥቃት በተሳተፍ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መንግስት የገባውን ቃል ኪዳን በማጠናከር የሚቀጥል ነው መባሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ላደረገችው ሰብዓዊ ድጋፍ እውቅና መስጠቱ ይታወሳል።