ቀጥታ፡

በጌዴኦ ዞን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል-ኪዳን ሰነድ ተፈራረሙ

ዲላ፤ ሚያዝያ 14/2013( ኢዜአ ) በስድስተኛ ጠቅላላ ምርጫ በጌዴኦ ዞን የሚወዳደሩ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫውን ሂደት ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሀዊ እንዲሆን ለማስቻል የቃል- ኪዳን ሰነድ ተፈራረሙ።

የቃል- ኪዳን ሰነዱን የተፈራረሙት ብልጽግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ እና የጌዴኦ ሕዝብ  ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ጌህዴድ/ ናቸው።

የቃልኪዳን ሰነዱ ፓርቲዎቹ በምርጫው ሂደት ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግሮችን የሚፈቱበትን፣ በቅስቀሳ ወቅት መደረግ ባለባቸው ጥንቃቄዎችና ቅሬታ አፈታት ዙሪያ የሚከተሏቸውን አካሄድ መያዙ ተገልጿል።

የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ጌዴኦ ዞን  ተወካይ አቶ ይመኑ ዳካ በወቅቱ እንዳሉት፤ ፓርቲዎቹ የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ ለመስራት የጋራ ምክር ቤት መስርተው እየሰሩ ይገኛል።

"የጋራ ምክር ቤቱ ፓርቲዎቹ ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ መንገድ በውይይት ለመፍታት የተፈራረሙት የቃል-ኪዳን ሰነድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል።

የጌዴኦ ሕዝብ  ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ጌህዴድ/ ተወካይ አቶ ታደለ ደጉ ፤ የቃል- ኪዳን ሰነዱ ያካተታቸው የማስፈጸሚያ ስልቶች ተቀባይነት ያላቸውና በቀጣይም በጋራ ለመስራት አጋዥ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ዜጎች በሚፈለገው ልክ የመራጭነት ካርድ እየወሰዱ አይደለም ያሉት አቶ ታደለ አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ አለመከፈትና አስቀድሞ መዘጋት በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች በመራጭነት መመዝገብ እንዳይችሉ ከፍተት መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ዜጎች ያሉ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም የመራጭነት ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት ካርድ በመውሰድ የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሐራዊ ምርጫ ቦርድ የጌዴኦ ዞን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ አበባየሁ  በበኩላቸው፤ በዞኑ በመራጭነት ይመዘገባሉ ተብሎ ከሚጠበቁ 563 ሺህ 654 ሰዎች መካከል  እስካሁን ካርድ የወሰዱት 48 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ማስተባበሪያው በየምርጫ ጣቢያው በመዘዋወር  በተለይ ከመታወቂያ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል በምርጫ ክልሉ ነዋሪ ስለመሆኑ በሶስት ምስክሮች እየተረጋገጠ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የቀረው ህብረተሰብ  ወጥቶ የመራጭነት ካርድ እንዲወስድ ሁሉም  ፓርቲዎች በቅስቀሳው ላይ ጠንካራ ስራ መስራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም