ለተመራቂ የጤና ባለሙያዎች የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት ሥምምነት ተደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
ለተመራቂ የጤና ባለሙያዎች የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት ሥምምነት ተደረሰ
ሚያዝያ 14/2013 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴርና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ተመራቂ የጤና ባለሙያዎችን በዘመናዊ ዘዴዎች ከቀጣሪዎች ጋር ለማገናኘት በጋራ ለመሥራት ተስማሙ።
በሥምምነቱ መሠረት ሁለቱ ተቋማት በጤና ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትና የአገር ውስጥና የውጭ አገር የሥራ ዕድሎችን ለማመቻቸት በጋራ እንደሚሰሩ ተገልጿል።
በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎች የራሳቸውን የጤና አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ እንዲመሰርቱ የመደገፍና የማበረታታት ሥራ በጋራ እንደሚሰሩም ነው የተጠቆመው።
ለዚህም የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ሥራ ፈላጊዎችን በመመዝገብና ሥልጠና በመስጠት በኩል የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተጠቅሷል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት፤ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ለሚወጡ የጤና ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው።
ይህም በአገር ውስጥና በውጭ ሥራ ለማስያዝ፤ በሌላ በኩል የጤና ባለሙያዎቹ በተናጠልም ሆነ በቡድን ሥራ እንዲፈጥሩ ትኩረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የጤና ባለሙያዎችን በአዳዲስ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለማሠማራት የሚያግዙ መመሪያዎች ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልጸዋል።
የጤና ባለሙያዎች የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ባዘጋጀው የበይነ-መረብ ምዝገባ በተቋሙ ድረ ገጽ በመግባት እንዲመዘገቡም ጠይቀዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ኮሚሽኑ ለጤና ባለሙያዎች የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት ከተለያዩ ተቋማት እንደሚያስተባብር ገልፀዋል።
"በተለይም የጤና ባለሙያዎች በተናጥልና በጋራ በመሆን ሥራ እንዲፈጥሩ ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁኔታዎችን ያመቻቻል" ብለዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በሁሉም ዘርፍ ሥራ ፈላጊዎችን መመዝገብ የሚያስችል መተግበሪያ ያዘጋጀ ሲሆን ሥራ ፈላጊዎች ከሚያዚያ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሚከተለው አድራሻ https://health-care.jccnrp.com በኦን ላይን መመዝገብ ይችላሉ ተብሏል።