ቀጥታ፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ የተሰጣቸውን የአየር ሠዓት በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም - መገናኛ ብዙሃን

ሚያዝያ 14/2013 (ኢዜአ) ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ በመገናኛ ብዙሃን የተሰጣቸውን ነፃ የአየር ሠዓት በአግባቡ እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል።

ውይይቱ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ነው።

በውይይቱ  እየተጠቀሙበት አለመሆኑ ተገልጿል።

ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የምርጫ ዴስክ ተወክለው የመጡ ሃላፊዎች እንደገለጹት በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ የተሰጣቸውን የአየር ሠዓት በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም።

ፓርቲዎቹ ከተሰጣቸው ነፃ የአየር ሠዓት እስካሁን የተጠቀሙት 51 ነጥብ 3 በመቶውን ብቻ እንደሆነም ተገልጿል።

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ኦ.ቢ.ኤን የምርጫ ዴስክ የተወከሉት አቶ አብዱልሰላም መሃመድ ጣቢያቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የአየር ሠዓት ድልድልን እንዲጠቀሙበት ዝግጅት አድርጎ እየጠበቀ መሆኑን አንስተዋል።

ይሁንና ከተወሰኑ ፓርቲዎች በቀር አብዛኞቹ በተሰጣቸው የአየር ጊዜ እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ከኢቢሲ የምርጫ ዴስክ የተወከሉት አቶ ገናናው ለገሰ በበኩላቸው ከመጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውንና የምርጫ ቅስቀሳ እንዲያካሄዱ መደረጉን አስታውሰዋል።

ጣቢያውም በቴሌቪዥንና በራዲዮ የሚተላለፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መልዕክቶቸ በአግባቡ እንዲተላለፉ ስቱዲዮ አዘጋጅቶና የሰው ሃይል አደራጅቶ  ለማስተናገድ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

የፓርቲዎቹ የምርጫ ቅስቀሳም በኢቲሺ ዜና ቻናል፣ በብሔራዊ ራድዮ፣ በኦሮምኛ፣ በአፋርኛና በሶማልኛ እንዲሁም በኢቲቪ ቋንቋዎች በአፋን ኦሮሞ እያስተላለፈ መሆኑን አንስተዋል።

ሆኖም በአየር ሠዓቱ የተጠቀሙ ውስን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም ውድ የሆነውን የሕዝብ ሃብት  የአየር ሠዓት በአግባቡ ያልተጠቀሙ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን አውስተዋል።

በተለይ በቤኒሻልጉል ጉምዝና በጋምቤላ ክልሎች የሚንቀሳቀሱና በጣቢያቸው የአየር ጊዜ የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመደበላቸው የአየር ሠዓት አጠቃቀም ላይ ሰፊ ክፍተት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።

"ለፓርቲዎቹ ከመጋቢት30 ጀምሮ መልዕክታቸውን እንዲያስተላልፉ ቀን በቀን እየደወልን ስናስታውሳቸው፣ ተገቢውን ድጋፍና ክትትልም ስናደርግ ቆይተናል" ነው ያሉት።

እስካሁን በጣቢያው ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዚያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም 1 ሺህ 905 ደቂቃ እንዲጠቀሙ ቢመደብም ጥቅም ላይ የዋለው 989 ደቂቃ ወይንም 51 ነጥብ 91 በመቶ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ይህ አሃዝ የሚያመለክተው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተሰጣቸውን የአየር ሠዓት በአግባቡ እየተጠቀሙበት አለመሆኑን ነው ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው በአየር ጊዜው ላለመጠቀማቸው የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርበዋል።

ከምክንያቶቻቸው መካከል የተመደቡላቸው የመገናኛ ብዙሃን የፓርቲዎቹ መቀመጫ የተለያየ አካባቢ መሆን፣ "ፕሮግራሞቻቹን ቀርጻችሁ አምጡ" መባላቸውና የበጀት እጥረት የሚሉት ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም ከ48 ሠዓታት በፊት ፕሮግራሞቻችሁን አቅርቡ ስለምንባል የጊዜ እጥረት አለብን ነው ያሉት።

ፓርቲዎቹ የመገናኛ ብዙሃኑ ቀረጻው በሚዲያዎቹ ቢያደርጉላቸው ችግሮቻቸውን እንደሚያቀሉላቸው በመግለፅ 'ይህ እንዲሆን ትብብር ይደረግልን' ሲሉ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ያሉነን ሃሳቦችና የፖሊሲ አማራጮች እንድናቀርብ የመገናኛ ብዙሃኑ በገልተኝነት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊተባበሩ ይገባል ሲሉም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ኢድሪስ ፓርቲዎች የተሰጣቸውን የአየር ሠዓት በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በአየር ሠዓት አጠቃቀም ላይ ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች እንደሚመለከቷቸው ገልጸው 'የመገናኛ ብዙሃኑ በትብብር መንፈስ እንዲሰሩ እናደርጋለን' ብለዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን ሃላፊ ሶሊያና ሺመልስም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለባቸውን የበጀት እጥረት ከግንዛቤ በማስገባት የመገናኛ ብዙሃኑ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣነ ከሁለት ሣምንት በፊት ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮችና ሃሳቦቻቸውን እንዲያቀርቡ ነፃ የጋዜጣ አምድና የአየር ጊዜ ድልድል ማድረጉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም