መንግሥት ምርጫውን ሠላማዊና ነጻ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደተሻለ ዴሞክራሲ ለማሻገር ቁርጠኛ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ምርጫውን ሠላማዊና ነጻ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደተሻለ ዴሞክራሲ ለማሻገር ቁርጠኛ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ
ሚያዚያ 14/2013 (ኢዜአ) መንግሥት ምርጫውን ሠላማዊና ነጻ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደተሻለ ዴሞክራሲ ለማሻገር ቁርጠኛ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ተናገሩ።
ከምርጫ በቀር ስልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ የሚደረግ ሙከራ 'የማይሳካ ከንቱ ሕልም ነው' ሲሉም ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር የመራጮች ምዝገባ ሂደትን በሚመለከት ውይይት አካሂደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሣምንት በፊት ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ምርጫውን በሚመለከት በበይነ መረብ አማካኝነት ከተወያዩ በኋላ የመራጮች ምዝገባ መሻሻል ማሳየቱ ተጠቁሟል።
በሲዳማና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች የመራጮች ምዝገባ ከ80 በመቶ በላይ አፈፃፀም መኖሩ በመድረኩ ተመላክቷል።
በሌሎች ክልሎችም የመራጮች ምዝግባ አፈፃፀም ከ50 በመቶ በላይ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በአፋር ክልል ከ453 ሺህ በላይ ሰዎች የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸው፤ በጋምቤላ ክልል የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ በመጀመሩ ምክንያት እስካሁን ያለው አፈጻጸም 41 በመቶ መሆኑም ተጠቅሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት እንዳይፈጠር የሚፈልጉ ኃይሎች ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን በውይይቱ ገልፀዋል።
ምርጫውን በማስተጓጎል፣ ደካማና የሚያዙት መንግስት ለመፍጠር ሌት ተቀን እየሰሩ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል ብለዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን የውስጥ ክፍፍል ያለው የመንግስት መዋቅር በመፍጠር ቀን ከሌት እየተጨቃጨቅን እንድንኖር ይሻሉም ነው ያሉት።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ ስልጣን የሚይዝ እንጂ የሚደራደርም ሆነ በሽግግር ስም የሚዳከም መንግስት አይኖርም ብለዋል።
ከዚህ በተቃራኒ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ሩጫ መንግስትን ከጀመረው አዲስ የዴሞክራሲ መንገድ አውጥቶ ወዳልተፈለገ ልምምድ ሊወስድ ስለሚችል መጠንቀቅ ይገባል ነው ያሉት።
መጪው ክረምት የኢትዮጵያ አንኳር ስራዎች የሚከናወኑበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግስት ድርብ ኃላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል።
የክልል መንግስታት ይህን ተገንዝበው ምርጫውን ሠላማዊና ነጻ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ዴሞክራሲ ለማሻገር ቁርጠኛ ሆነው እንዲሰሩም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያን ማሻገር ቁልፍ ግባችን መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እያንዳንዱ ዜጋ ተጠቃሚ የሚሆነው ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና መውጣት ስትችል መሆኑን አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ዜጎች ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም በቀረው የምዝገባ ጊዜ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ እንዲወስዱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት የቦርዱን ቀጣይ ስራዎች ለማገዝ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።