ለምርጫ አለመመዝገብ በእኛ ጉዳይ ላይ ሌላው እንዲወስን መፍቀድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለምርጫ አለመመዝገብ በእኛ ጉዳይ ላይ ሌላው እንዲወስን መፍቀድ ነው

አዳማ ሚያዝያ 14/2013 (ኢዜአ) ለምርጫ አለመመዝገብ በእኛ ጉዳይ ላይ ሌላው እንዲወስን መፍቀድ ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የኦሮሚያ ከፍተኛ አመራር ወይዘሮ ሎሚ በዶ አስታወቁ።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ኮንፈረንስ ዛሬ በአዳማ ገልማ አባገዳ ተካሂዷልደ።

የሊጉ ሊቀመንበር ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን በወቅቱ እንደገለጹት ኮንፈረንሱ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሀገርን በብልጽግናና በልማት ማስቀጠል የሚችል ፓርቲ በአሸናፊነት እንዲወጣ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጉላት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
ሰላም ሲጠፋና ሀገር ሲተራመስ የመጀመሪያ ተጎጂ የሚሆኑት ዜጎች መሆናቸወን የገለጹት ወይዘሮ ሰዓዳ "የማህበረሰብ ግማሽ አካል የሆነው ሴቶች የሰላም ባለቤቶች እኛው ነን ፤በማለት ለምርጫው ሰላማዊነት የበኩላችንን ሚና እንድንወጣ በኮንፍረንሱ መገባባት ላይ ደርሰናል" ብለዋል ።
"አሁን ያለው የሰላም መደፍረስ ብልጽግና ሀገር መምራት አይችልም ፤ለማስባል በጸረ ሰላም ሃይሎች የሚደረግ ሴራ በመሆኑ እኛ ሴቶች ይህን መሰል እንቅስቃሴዎችን በመደራጀት መመከት አለብን" ሲሉም ተናግረዋል ።
የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የኦሮሚያ ከፍተኛ አመራር ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው ሴቶች ያለፉትን ጨቋኝ ስርዓቶች ለመገርሰስ ያደረጉት ትግል ታሪክ የማይረሳው መሆኑን ገልጸዋል።
"ለውጡን ለማስቀጠልና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማምጣት የሚሆነንን ፓርቲ መምረጥ አለብን" ያሉት ወይዘሮ ሎሚ "አለመምረጥ በራሳችን ጉዳይ ላይ ሌላው እንዲወስን መፍቀድ ነው" ብለዋል።
ሴቶች ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ህብረተሰብ ድረስ በምርጫው በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡት የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎችም "ሴቶች በፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደምንችል ለማሳየት ዘንድሮ በሚካሄደው ምርጫ ተስትፎችንን ማጠናከር ይገባናል" ብለዋል።
ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የመጡት ወይዘሮ ሰዒዳ አምድሁን የሴቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር ኮንፍረንሱ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
"ምርጫው በተለይም እኛ ሴቶችን ይመለከታናል" የሚሉት ደግሞ ከሀረር መጥተው የተሳተፉት ወይዘሮ ኩኑዛ ሀሰኔ ናቸው።
ከቀበሌ ጀምሮ በክልሉ በየደረጃው ሲካሄድ በነበረው የሴቶች ሊግ ኮንፈረንስ ወደ 5 ሚሊየን ሴቶች የተሳተፉበት እንደነበር በመድረኩ ተወስቷል።
ዛሬ በክልል ደረጃ በተካሄደው ኮንፈረንስም ከወረዳ ፣ ከዞንና ከክልል እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሊጉ አመራሮችና አባላት የተሳተፉበት ነው።