የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ያስገነባውን ትምህርት ቤት አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ያስገነባውን ትምህርት ቤት አስመረቀ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 14/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ከ10ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ በአዲስ አበባ ያስገነባውን የቅድመ መደብኛ ትምህርት ቤት አስመረቀ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ከህይወት የተቀናጀ የልማት ድርጅት ጋር በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የቅድመ መደብኛ (አፀደ ህፃናት) ትምህርት ቤት ገንብቶ አስመርቋል።
በክፍለ ከተማው ወረዳ ስድስት ወይራ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ1 ሺህ 600 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድርግ ነው ያስገነባው።
ትምህርት ቤቱ 8 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ሲሆን 400 ተማሪዎን ተቀብሎ ማስተማር ጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፅጌረዳ ታፈሰ እንደተናገሩት ትምህት ቤቱ የተገነባው ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናትና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ልጆች የትምህርት እድል ለማመቻቸት ነው።፡
ትምህትረት ቤቱ ከማስተማር ባለፈም ነፃ የምግብ፣ የህክምና እና ሌሎችንም አገልገሎቶች ይሰጣል ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሮችና በክልሎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ህፃናት የትምህርት እድል እንዲያገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የህይወት የተቀናጀ የልማት ድርጅት ስራአስኪያጅ ሲስተር ጥበበ መኮ ቡሉ በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ መገንባት ለብዙ ታዳጊ ልጆች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ወላጆቻቸውን ላጡ እና ቤተሰቦቻቸው በዝቅተኛ ኑሮ ሚያስተዳድሯቸው ልጆች የትምህርት እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ ህፃናትን ከማስተማር ባለፈም ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ህፃናት የትምህርት ዕድል ዕንዲያገኙ ዳያስፖራው ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።