ቀጥታ፡

በሶስት ሳምንት ውስጥ ከ6 ሺህ ከረጢት በላይ የ “ኦ” የደም ዓይነት ተሰበሰበ

ሚያዚያ 14 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት በሶስት ሳምንት ውስጥ ከ6 ሺህ ከረጢት በላይ የ “ኦ” የደም ዓይነት መሰብሰቡን አስታወቀ።

አገልግሎቱ "ኦ" የተሰኘው የደም አይነት እጥረት ገጥሞት "ደም ለጋሾች ድረሱ" የሚል ጥሪ ለህብረተሰቡ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።

ለጥሪው ፈጣን ምላሽ ያገኘው አገልግሎቱ፤ በሶስት ሳምንት ውስጥ ከ6 ሺህ ከረጢት በላይ “ኦ” የደም ዓይነት በመሰብሰብ ክምችቱን ወደ 15 ቀናት ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጿል።

በብሔራዊ የደም ባንክ የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ተመስገን አበጀ፤ በኢትዮጵያ ካሉት የደም አይነቶች ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆነው በሳይንሳዊ አጠራሩ "ኦ" እየተባ የሚጠራው ነው።

የደም አይነቱ ለሌሎች የደም አይነት ላላቸው የሚሰጥና ለራሱ ከሌሎች የማይቀበል መሆኑ እጥረት ሊፈጠር እንደቻለ ገልጸው፤ ጥሪ የተደረገለት ህብረተሰብ ፈጣን ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን ያለው ክምችት ለ15 ቀናት ብቻ ስለሆነ ልገሳው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ደም ባንኮች 340 ሺህ የደም ከረጢት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም ዶክተር ተመስገን ጠቁመዋል፡፡

እንደእሳቸው ገለጻ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 257 ሺህ ከረጢት ደም 211 ሺህ ከረጢት ከለጋሾች ተሰብስቧል፡፡ 

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ መደፍረስ ችግር በበጀት ዓመቱ ደም ባንኮች በሙሉ አቅማቸው እንዳይንቀሳቀሱ ጫና ማሳደሩንም ጠቁመዋል።

"በአዲስ አበባ ልደታ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም በመገናኛ፣ ሜክሲኮ እና አራት ኪሎ አደባባዮች ላይ ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል" ያሉት ዶክተር ተመስገን፤ በክልሎች ያሉ ደም ባንኮች በበቂ ሁኔታ ከህብረተሰቡ ደም መሰብሰብ እንዲችሉ ግብአቶች ከማሟላት በተጨማሪ የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም