ቀጥታ፡

በ"8100-ኤ" አጭር መልዕክት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ 122 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 14/2013 (ኢዜአ )ኢትዮ-ቴሌኮም ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በ"8100-ኤ" አጭር የፅሁፍ መልዕክት ከደንበኞቹ የሰበሰበውን ከ122 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስረከበ።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራአስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ከደንበኞች የተሰበሰበውን ገንዘብ ዛሬ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ለአቶ አሸብር ባልቻ አስረክበዋል።

ቴሌኮሙ ለግድቡ ግንባታ በ8100-ኤ በሶስት ዙር ከደንበኞቹ በአጠቃላይ 252 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገልፀዋል።

ለዚህ ስኬት የኢትዮ-ቴሌኮም ደንበኞች ላበረከቱት አስተዋፅኦም ምስጋና አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ቴሌኮሙ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተቋሙና በሠራተኞቹ ስም የ111 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ መፈፀሙን አስታውሰዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔም ሕዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ከግድቡ ግንባታ ጅማሬ እስካሁን ከኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በልገሳ መሰብሰቡንም ገልፀዋል።

ዶክተር አረጋዊ የ8100-ኤ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በግድቡ ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን እንዲያሳርፍ ዕድል የከፈተ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የሕዳሴው ግድብ የሉዓላዊነት፣ የአንድነትና የፍትሃዊነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት በመሆኑ ዜጎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩም ነው ያሳሰቡት፡፡ 

ግድቡ ከኢትዮጵያ ባሻገር የአፍሪካም ኩራት እንደሆነ ዶክተር አረጋዊ ተናግረዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም በ8100-ኤ አጭር የጽሑፍ መልዕክት በመላክ ከፍተኛ ተሳትፎ ላደረጉ 20 ግለሰቦች ዕውቅና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም