በመዲናዋ በግንባታ ላይ የሚገኙ 38 መንገዶች በዚህ ዓመት ለትራፊክ ክፍት ይሆናሉ -- የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በግንባታ ላይ የሚገኙ 38 መንገዶች በዚህ ዓመት ለትራፊክ ክፍት ይሆናሉ -- የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን
አዲስ አበባ ሚያዝያ 14/2013 (ኢዜአ)በአዲስ አበባ በግንባታ ላይ ያሉ 38 የአስፋልት መንገዶችን በበጀት ዓመቱ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲል የየከተማዋ መንገዶች ባለሥልጣን ገለፀ።
የባለሥልጣኑ የዕቅድ በጀትና ስትራቴጂክ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ከመንገዶቹ መካከል 22ቱ በራስ ኃይልና 16ቱ በሥራ ተቋራጮች እየተገነቡ ነው።
መንገዶቹ 85 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ሲሆኑ ግንባታቸው 4 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ይከወናል።
በራስ ኃይል እየተገነቡ ያሉት መንገዶች መካከል ከወሎ ሰፈር-ኡራኤል፣ ከቀጨኔ-ቁስቋም፣ ከጉራራ ኪዳነምህረት-ፈረንሳይ አቦ፣ ከዋሽንግተን አደባባይ እስከ ለገሃር ያሉት እንደሆኑ ሃላፊው ጠቁመዋል።
ከንፋስ ስልክ ላፍቶ አንበሳ ጋራጅ፣ ከሃና ማርያም ዳማ ሆቴል ላፍቶ ሚካኤል፣ ከአጎና ሲኒማ ሴኔጋል ኤምባሲ፣ ከኮተቤ አማኑኤል በራስ ኃይል የሚገነቡት አብዛኛው ሥራቸው የተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ለትራፊክ ክፍት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
ከመገናኛ ውሃ ልማት ወረዳ 17፣ ከቦሌ ቡልቡላ ሎት አንድና ሁለት በስራ ተቋራጭ እየተገነቡ ካሉ መንገዶች መካከል መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከቄራ-አብነት-ጎፋ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም፣ ከሽሮሜዳ-ቁስቋም፣ ከራስ ደስታ-ቀጨኔ ስምንት ቁጥር ማዞሪያ፣ ከሲኤምሲ ወንድይራድ ትምህርት ቤት ጎሮ ፕሮጀክቶችንም ዘንድሮ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።
ከአራራት ሆቴል ኮተቤ ካራ ሎት አንድና ሁለት የዘገየ ፕሮጀክት መሆኑን የገለፁት አቶ አዲሱ አንደኛው ሎት ከሥራ ተቋራጩ ውሉ ተቋርጦ ግንባታው በራስ ኃይል እንዲካሄድ መሰጠቱን ገልፀዋል።
ይህ ፕሮጀክት አብዛኛው ሥራው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ግንባታው በቀንና በምሽት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠናቀቁት አምና የተጀመሩ እንዲሁም ግንባታቸው በ2009 ዓ.ም የተጀመሩና ረጅም ጊዜ የፈጁ መንገዶች መሆናቸውን ገልፀዋል።
በፕሮጀክቶቹ ግንባታ የሚያጋጥሙ የወሰን ማስከበር ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
መንገዶቹ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የእግረኛ መንገድና የመንገድ መብራት ተሟልቶላቸው የሚገነቡ ናቸው ብለዋል።
የመንገዶቹ መጠናቀቅ የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት በማሳለጥ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር አካባቢዎቹን በማነቃቃት የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የላቀ መሆኑንም ነው አቶ አዲሱ የገለፁት።