ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ላሉ በርካታ ችግሮች የውጭ ሃይሎች የማይታዩ እጆች አሉበት

ሚያዚያ 14/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ላሉ በርካታ ችግሮች የውጭ ሃይሎች የማይታዩ እጆች ያሉበት በመሆኑ የጥፋት መሳሪያ ባለመሆን የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ደህንነት በጋራ መጠበቅ እንደሚገባ አቶ ኤሊያስ ወንድሙ ገለፁ።

አቶ ኤሊያስ ወንድሙ የፀሃይ አሳታሚ ድርጅት መሥራችና ከአርትዖት ዳይሬክተርነታቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካሪም ናቸው።

የዓለም አቀፉ የስትራቴጂክ ጥናት ማኅበርም አባል፣ የዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ጥናት መጽሄት መሥራችና አርታኢ እንዲሁም በአሜሪካ ሎሳንጀለስ የመጽሃፍ ግምገማ ላይም በአራታኢነት ይሳተፋሉ።

አቶ ኤሊያስ ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ ብቅ ባሉበት አጋጣሚ በኢትዮጵያ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በአስተያየታቸውም እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰቱ ላሉ በርካታ ችግሮች የተለያዩ የውጭ ሃይሎች የማይታዩ ስውር እጆች አሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ይህንን በአግባቡ በመረዳት ለአገራቸው ህልውና፣ ለህዝባቸው ሰላምና ደህንነት በጋራ ሊቆሙ ይገባል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሁሉም ጊዜያት የውጭ አካላት ተፅዕኖዎች ከአፄ ቴድሮስ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስካሁንም የበረቱ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በተለይ ሃያላን አገራት የእርስ በእርስ ሽኩቻቸውን ቂም የሚወጡት በአፈሪካ አገራት የውክልና ጦርነት መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ያሉ አገራት እንዳያድጉ እና እንዳይለሙ የግጭት ቀጣና ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ አገራት በሌሎች አገራት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ጉዳያቸውን ለማስፈፀም አንዱ ሌላውን በማገዝ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር እያደረጉ ነው ይላሉ አቶ ኤሊያስ።

በተለይም በኢትዮጵያ አሁን ላይ ሲታይ የራሳችንን ንቀን የውጭውን የተቀበልንበት መንገድ ለውድቀትና የከፋ ግጭት ሊዳርገን ስለሚችል ሁላችንም ልናስብበት ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ዘመናዊ ትጥቅ የነበረውን ወራሪ ሃይል ድል የተጎናፀፈችው በአንድነቷ እና በህዝቦቿ ጀግንነት መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም አሁን በተለያዩ ዘመናዊና ስውር መንገዶች በመውጋት ሀገር ለመበታተን የሚጥሩትን ሁሉ መመከት እንጂ የጥፋት መሳሪያ መሆን አይገባም ብለዋል።

በተለይ ምሁራን የኢትዮጵያን እድገት፣ ሰላምና ልማት እውን ለማድርግ በጥናት የተደገፈ መፍትሄ በማምጣት አገራቸውንና ህዝባቸውን ከጥፋት መታደግ አለባቸው ነው ያሉት።

አሁን ላይ እየተፈጠሩ ያሉ እንቅፋቶችንና የችግሮቹን መሰረት መረዳት ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ኤሊያስ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታዩ ላሉት በርካታ ችግሮች የውጭ ሃይሎች ስውር እጆች መኖራቸውን አብራርተዋል።

በመሆኑም ሁሉም የውጭ ሃይሎች የማይታዩ እጆች የጥፋት መሳሪያ ባለመሆን የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ደህንነት በጋራ መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት።

የችግሮቹን ሁሉ መንስኤ ጠንቅቆ በመረዳት በተለያዩ ግጭቶች አገሪቷን ችግር ውስጥ መክተትና ህዝቦቿን ለችግር ከሚዳርጉ ተግባራት ሁሉም ሊጠነቀቅ ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በክብሯና በአንድነቷ ፀንታ እንድትቀጥል ሁላችንም በጋራ እንቁም ሲሉ መልእክታቸውን ለመላው ህዝብ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም