ቀጥታ፡

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የእግር ኳስ ውድድር እንዲያጫውት ተመረጠ

ሚያዝያ 13/2013(ኢዜአ) ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በቶኪዮ ኦሊምፒክ የእግር ኳስ ውድድር እንዲያጫውት መመረጡን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

32ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር ከሐምሌ 14 እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።ውድድሩ በ33 የስፖርት አይነቶች የሚካሄድ ሲሆን ከውድድሮቹ አንዱ በሁለቱም ጾታዎች የሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ነው።

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በቶኪዮ ኦሊምፒክ የእግር ኳስ ውድድሮችን እንዲያጫውቱ ዛሬ ይፋ ካደረጋቸው የዋና ዳኞች ዝርዝር ውስጥ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ መካተቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ባምላክ በኦሊምፒክ የእግር ኳስ ውድድር ሲያጫውት የቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጀመሪያው ነው።

እ.አ.አ በ2009 ኢንተርናሽናል ዳኛ የሆነው የ40 ዓመቱ ባምላክ ተሰማ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የብሔራዊ ቡድንና የክለቦች ውድድሮች ላይ ጨዋታዎችን በመምራት የረጅም ጊዜ ልምድ አካብቷል።

ባምላክ እ.አ.አ በ2018 በሩሲያ አስተናጋጅነት በተካሄደው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በረዳት ዳኝነት ኢትዮጵያን መወከሉ የሚታወስ ነው።

የቶኪዮ ኦሊምፒክ የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ከሐምሌ 14 እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲሁም የሴቶች የእግር ኳስ ውድደር ደግሞ ከሐምሌ 14 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።

በወንዶች 16 በሴቶች 12 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።እ.አ.አ በ2020 ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው 32ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ አመት መራዘሙ ይታወሳል።

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከ200 አገራት በላይ የተወጣጡ ከ11 ሺህ በላይ ስፖርተኞች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም