ቀጥታ፡

በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ቡድን ተሸነፈ

ሚያዝያ 13/2013 (ኢዜአ)  በአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ቡድን በመጀመሪያው ጨዋታው ሽንፈት ገጥሞታል።

በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን አዘጋጅነት 32ኛው የአፍሪካ የሴቶች ክለቦች ውድድር ዛሬ በቱኒዚያ ተጀምሯል።

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ቡድኖች ኢትዮጵያን ወክለው ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ።

በምድብ አንድ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከብሩንዲው ሙዚንጋ፣ ከኬንያው ኬንያ ፕሪዝንስ እንዲሁም ከቱኒዚያዎቹ ሲኤስ ሰፋክሲያንና ኬሊቢያ ክለቦች ጋር ተመድቧል።

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በምድብ ሁለት ከቱኒዚያው ካርቴጅ፣ ከናይጄሪያው ከስተምስ፣ ከኮትዲቭዋሩ አሴክ ሚሞሳስ፣ ከኬንያ ኬንያ ፕሪዝስንና ከሴኔጋሉ ኤኤስ ዱዋኔስ ክለቦች ጋር ተደልድሏል።

ዛሬ ረፋድ ላይ በተደረገው የመክፈቻ ጨዋታ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በናይጄሪያው ከስተምስ በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ (25 ለ 12፣ 25 ለ17 እና 25 ለ 16) በድምሩ ሶሰት ለዜሮ ተሸንፏል።

ሌላኛው የውድድሩ ተሳታፊ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ30 ከሲኤስ ሰፋክሲያን ጋር ይጫወታል።


በደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሊጉን እየመራ ሲሆን ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

የአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ክለብ ውድድር እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ይቆያል።

ኢትዮጵያ በሴቶች ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች የተሳተፈችው ከአምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች አማካኝነት ነበር።

በተያያዘ ዜና 39ኛው የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ከሚያዚያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

በውድድሩ ኢትዮጵያን ወክሎ በምድብ ሶስት የተደለደለው ወላይታ ዲቻ በምድቡ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በቱኒዚያ ኬሊቢያ፣ በታንዛኒያው ኤምቲሲና በዩጋንዳው ኔሞ ስታርስ ተሸንፏል።

ወላይታ ዲቻ ከ9 እስከ 16 ያለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ውድድር ነገ ከሩዋንዳው ሩዋንዳ ኢነርጂ ጋር ይጫወታል።

ኢትዮጵያን በውድድሩ ላይ ወክሎ ይሳተፋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሆቴልን ጨምሮ ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን ያቀረበው የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ በመዘግየቱ በውድድሩ ላይ ሳይሳተፍ ቀርቷል።

በወንዶች ውድድር የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ።

የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ከኬንያው ጂኤስዩ፣ የግብጹ ዛማሌክ ከኬንያው ኬንያ ፒኤ፣ የሊቢያው ስዌህሊ ከዩጋንዳው ኔሞ ስታርስ እንዲሁም የቱኒዚያው ኬሊቢያ ከካሜሮኑ ፖርት ክለብ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር እ.አ.አ በ1980 የተጀመረ ሲሆን የግብጹ አልሀሊ 14 ጊዜ፣ የቱኒዚያው ሲኤስ ሰፋክሲያን ስድስት እንዲሁም የግብጹ ዛማሌክ አምስት ጊዜ አሸናፊ ሆነውበታል።

ከእ.አ.አ በ1986 ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር የግብጹ አልሀሊ 10 ጊዜ፣ የኬንያዎቹ ክለቦች ኬንያ ፓይፕላይንና ኬንያ ፕሪዝንስ በቅደም ተከተል ስድስትና አምስት ጊዜ አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም