የመንግስት የመሬት ይዞታ ህጋዊ የካዳስተርና ሰርተፊኬት ዝግጅት ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የመሬት ይዞታ ህጋዊ የካዳስተርና ሰርተፊኬት ዝግጅት ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13/2013 (ኢዜአ) የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የፌዴራል መንግስትና የልማት ድርጅቶችን የመሬት ይዞታ ህጋዊ የካዳስተርና ሰርተፊኬት ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የመንግስት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች የመሬት ይዞታ ህጋዊ ካዳስተርና ሰርተፊኬት ዝግጅትን በትብብር ለመስራት እንደሚያስችላቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ጂኦሽስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻህ፤ የፌዴራል መንግስት የመሬት ይዞታዎች በትክክል የት እንደሚገኙና መጠናቸው ምን ያህል እንደሆነ በመለየት የመሬት አጠቃቀም ካርታ ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በተለያዩ ቦታዎች የመሬት ቅየሳና አጠቃቀም ካርታ ዝግጅት በማካሄድ የፌደራል መንግስት የመሬት ይዞታዎች ምዝገባ መካሄዱን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ዘሪሁን አምደ-ማርያም እንዳሉት በመዲናዋ ወደ 280 ሺህ የሚሆኑትን ይዞታዎች በካዳስተር በመመዝገብ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።
የፌደራል መንግስት የመሬት ይዞታዎችን በዘመናዊ የካዳስተር ስርዓት መመዝገብም በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ከፍተኛ መተማመን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ስምምነቱም የፌደራል መንግስት የመሬት ይዞታዎችን ከአስተዳደሩ ይዞታዎች ጋር በማስተሳሰር በቅየሳ፣ በአቅርቦትና በከተማ ማደስ ስራዎች ግልጽና ፈጣን አሰራር ለመዘርጋት ያስችላል ብለዋል።
የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን፤ ስምምነቱ ኮርፖሬሽኑ የፌደራል መንግስትና የልማት ድርጅቶችን የመሬት ይዞታዎች በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር የሚያስችለው መሆኑን ገልጸዋል።
መረጃን መሰረት ያዳረገ የመሬት ካዳስተር ምዝገባ በማካሄድ ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለው ስርዓት በመፍጠር አልሚዎችን ለማስተናገድ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
በአገሪቱ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም 50 በመቶ የሚሸፍነውን ሉዓላዊ ግዛት የአየር ፎቶግራፍ መረጃ ማሰባሰብ እንደተቻለ ተመላክቷል።
ይህም የፌደራል መንግስትና የልማት ድርጅቶች የመሬት ይዞታ ህጋዊ ካዳስተርና ሰርተፊኬት እንዲኖራቸው እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።
የመሬት ይዞታና አስተዳደር ስርዓቱን በዘመናዊ መልኩ ለመምራትና ለማስተዳደር ተቋማቱ በትብብር መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን፤ የፌደራል መንግስትና የልማት ድርጅቶች የመሬት ይዞታን በህጋዊና ተገቢ መንገድ ለማስተዳደር እንዲቻል በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 መቋቋሙ ይታወቃል።