ቀጥታ፡

"ለኢትዮጵያ እንቁም" የሚል ግብረ ኃይል በአውሮፓ ተቋቋመ

ሚያዚያ 1/ 2013 (ኢዜአ) የአውሮፓ አንዳንድ የፓርላማ አባላትና መንግስታት እያስተጋቡ ያሉትን የተዛቡ መረጃዎች ለመከላከል ለኢትዮጵያ እንቁም (Defend Ethiopia) የሚል ግብረ ኃይል ተቋቋመ፡፡

ግብረ-ኃይሉ በዲፕሎማሲ እና በሎቢ፣ በማህበራዊና በአለም ዓቀፍ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለውን ሀሰተኛ መረጃ ለማረምና በሎጅስቲክስ ማሰባሰብ ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡

ግብረ ኃይሉ ከሰባ በላይ ከፍተኛ ምሁራንና ወጣት የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችን የያዘ ሲሆን በመንግስት ላይ ያነጣጠሩ አሉታዊ ጫናዎችን በመቀነስ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን ሁለገብ የለውጥ ሂደት ለማገዝ ያለመ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ግብረ ሃይሉ በአውሮፓ ደረጃ ተጠናክሮ እና ተቀናጅቶ ከቀጠለ የፓርላማ አባላት፣ ቲንክ ታንክ ቡድኖች እና አለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በቀላሉ ለመቀነስ ያስችላል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያዊያኑና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በበኩላቸው የዲጂታል ዲፕሎማሲና የሎቢ ዘመቻው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ቃል ገብተዋል።

በዚህም የዘመኑ መረጃ ፈጣን እና ጊዜን የማይጠይቅ በመሆኑ ሳያቋርጥ መረጃ ሊያቀብል የሚችል ማዕከል እንዲፈጠር መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም