ኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ ጀመረ
ደሴ ፤ ሚያዚያ13 /2013(ኢዜአ) በኮምቦልቻ ከተማ 172 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባው ጠቅላላ ሆስፒታል የሰው ሃይልና የህክምና ቁሳቁስ በማሟላት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አስታወቁ።
ስራ አስኪያጁ አቶ ከበደ ይመር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሆስፒታሉ ግንባታ ከመጓተቱም ባለፈ ጥር ወር 2013ዓ.ም. ቢመረቅም በወቅቱ የህክምና ግብዓትና የሰው ኃይል ባለመሟላቱ ምክንያት ወደ ስራ መግባት ሳይቻል ቆይቷል።
በዚህም በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ እንደነበር አውስተዋል።
አሁን ላይ ከክልል መንግስትና ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ጥረት የሰው ሃይልና የህክምና ቁሳቁስ ተሟልቶለት የህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።
ሆስፒታሉ 163 የጤና ባለሙያና አስተዳደር ሰራተኞች ቅጥር እንደተፈጸመ ጠቅሰው፤ ከመካከላቸውም
10 ጠቅላላና ሶስት ስፔሻሊስት ሐኪሞች ይገኙበታል ብለዋል።
ህሙማን ተኝተው የሚታከሙበት 200 አልጋዎችና የላቦራቶሪ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች እንደተሟሉለትም ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
ከኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ መሰረት ይማም በሰጡት አስተያየት፤ የሆስፒታሉ ግንባታ መጓተቱና ከተጠናቀቀ በኋላ ተመርቆም ስራ አለመጀመሩ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል።
ችግሩ አልፎ አሁን ስራ በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸው ፤ በአቅራቢያቸው የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ የደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ሸዋ ዞኖችና አፋር ክልል ህዝብ ተደራሽ በመሆን እንደሚያገለግል ተመልክቷል፡፡