ቀጥታ፡

በሃድያ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከል 110 ሚሊዮን ችግኝ ተዘጋጀ

ሆሳዕና፤ ሚያዚያ 13/2013 (ኢዜአ) በሀድያ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከል 110 ሚሊዮን ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ገለጸ።

የተዘጋጀው ችግኝ የቁጥር ብዛት ከአምናው ጋር ሲነፃጸር  25 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል።

ከ400 በሚበልጡ  ችግኝ  ጣቢያዎች ከተዘጋጀው ውስጥ በአብዛኛው ለምግብነት  የሚያገለግሉ  የፍራፍሬና አፈር መሸርሸር የሚከላከሉ ሀገር በቀል  ዝርያ  መሆኑን  የመምሪው ኃላፊ አቶ እዮብ ጩፋም ለኢዜአ ተናግረዋል።

በተለይ  በዞኑ የተመናመነውንና የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የቀርከሃ ምርት መልሶ ለማልማት የሚያስችል ዝግጅት በዘንድሮው የችግኝ ተከላ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

አምና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከለው 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኝ ውስጥ ህብረተሰቡ ባደረገው እንክብካቤ  97 በመቶው መጽደቁን  አስታውሰው ዘንድሮም እንደ ሀገር በዘርፉ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ሰፊ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።

የዞኑ የአካባቢ ጥበቃ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ክብሩ ኤርመኮ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ተግባራዊ ለማድረግ  በተደረገው  ርብርብ የዞኑን የደን ሽፋን ማደጉን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በልዩ  ትኩረት በችግኝ ተከላና እንክባካቤ ላይ የነቃ  ተሳትፎ  በማድረጉ  በዘርፉ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም የተራቆተ መሬትን  መልሶ እንዲያገግምና የአፈር ለምነት እንዲጨምር ብሎም  በአየር ንብረት ለውጡም አንጻራዊ ለውጥ እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።

በዞኑ ሌሞ ወረዳ የኃይሴ ቀበሌ  አርሶ አደር ሞሊሶ ሰላሙ በሰጡት አስተያየት፤  ከዚህ በፊት የተፈጥሮ ሀብቱ በመመናመኑ ብዙ ደክመው በሄክታር 15 ኩንታል  ስንዴ ብቻ ያገኙ እንደነበር አውስተዋል።

ባለፉት ዓመታት ለችግኝ ተከላ ትኩረት ተሰጥቶት ርብርብ ከተደረገ ወዲህ ምርታማነታቸውን በእጥፍ በማሳደግ ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል።

አሁን ላይ ችግኝ ተከላው ለውጥ እያመጣ በመሆኑ ዘንድሮም  በግላቸው   ከ100 በላይ ችግኝ  ለመትከል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለጥላ እና አፈር መሸርሸርን ከመከላከል ባለፈ ለምግብነት የሚውሉ ተክሎችን በመትከል ተጠቃሚ እንደሆኑ የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የቀበሌው ነዋሪ  ወይዘሮ ሲጎ አበበ ናቸው።

ከዚህ ቀደም የአካባቢያቸው መሬት መራቆት ለሚያረቧቸው እንስሳት  መኖና ውሃ ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው  የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በመንግስት ትኩረት ማግኘቱ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።

አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በየዓመቱ 50 ችግኝ በመትከል መሳተፋቸውን ያመለከቱት ፤ ወይዘሮ ሲጎ ፤ዘንድሮም  በግላቸው   100 ችግኝ  ለመትከል ማቀዳቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም