ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብ ድርድር ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣ የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የለውም- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብ ድርድር ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣ የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የለውም- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
ሚያዚያ 13/2013 (ኢዜአ) ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብ ድርድር ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣ የሚያደርጉት ጥረት በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው ትኩረት ካደረጉባቸው ጉዳዮች መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን ይመለከታል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እየተካሄደ ባለው ውይይት ኢትዮጵያ በማይናወጥ አቋሟ መቀጠሏን ገልጸው ግብፅና ሱዳን ግን ጉዳዩ ከህብረቱ አደራዳሪነት እንዲወጣ እየጣሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ መጻፏንም ተናግረዋል።
በሶስትዮሽ ድርድሩ ግብፅና ሱዳን ጉዳዩ ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣ ጫና እያደረጉ በመሆናቸው ምክር ቤቱ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ እንዲያደርግ በደብዳቤው ተመልክቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ፤ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊያን መፈታት ይችላሉ የሚል የፀና አቋም ስላላት የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል እየሰራች መሆኑን አረጋግጠዋል።
ግብፅና ሱዳን የድርድር ሂደቱን ከአፍሪካ ህብረት ለማስወጣት የሚያደርጉ ጥረት በኢትዮጵያ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
የሱዳንና ኢትዮጵያን የድንበር ጉዳይ አስመልክተውም ኢትዮጵያ ለሰላማዊ መፍትሔ ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከሰሞኑ ሱዳን 61 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዛ ለቃለች በሚል የሚናፈሰው ወሬም ከእውነታ የራቀ እና ፍጹም ሃሰት መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሠላማዊ መንገድን ብቻ አማራጭ በማድረግ የሁለቱ ሀገራት የድንበር ጉዳይ በሰላም እንዲፈታ ትሻለች ጥረቷንም ትቀጥላለች ብለዋል።