ቀጥታ፡

ንጹሃንን በሚገድሉ፣ በሚያፈናቅሉና ንብረታቸውን በሚያወድሙ አካላት ላይ መንግስት ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ

ሚያዚያ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) መንግስት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ንጹሃንን በሚገድሉ፣ በሚያፈናቅሉ፣ ሃብት ንብረታቸውን በሚዘርፉና በሚያወድሙ አካላት ላይ ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ "ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በኖርዲክ ሀገራት" የተሰኘ ድርጅት ጠየቀ።

ድርጅቱ የኢትዮጵያን ችግሮች በመለየት በሙያቸው ለማገዝ የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የመሰረቱት ነጻና ገለልተኛ ድርጅት መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አሳውቋል።

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ላይ ሙያዊ አበርክቶ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ፤ ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ አስመልክቶ ለኢትዮጵያ መንግስት ሃሳቡን በደብዳቤ አሳውቋል።

በዚህም "የኢትዮጵያን ሁኔታ በተለያዩ መረጃዎች ስንከታተል የፀጥታ ስጋት፣ የንጹሃን ሞት፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችና የንብረት ውድመትና የዜጎች መፈናቀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል፤ እኛንም አሳስቦናል" ብሏል።

"ችግሩ አድማሱን እያሰፋ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በተደራጁ ኃይሎች በተቀናጀና በከባድ መሳሪያ በተደገፈ ጥቃት የሰው ህይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙን እናወግዛለን" በማለትም ገልጿል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ በተነሳው ግጭትም የንጹሃን ደም ፈስሷል፣ መፈናቀልና ከፍተኛ የሆነ የንብረትና የተቋማት ውድመት መድረሱን አረጋግጠናል ሲልም በመግለጫው ጠቅሷል።

"በንጹሃን ዜጎች ላይ ከደረሰው ጉዳት አንጻር የመንግስት ህግ የማስከበር ሂደት መታየት አለበት" በማለት አመልክቷል።

"በኢትዮጵያ ያለውን መጠነ ሰፊ ችግር እንረዳለን" ያለው መግለጫው፤ "ነገር ግን የመንግስት ቀዳሚ ኃላፊነት ህግ ማስከበር በመሆኑ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ ህግ በማስከበር ለዜጎች ከለላና የሰላም ዋስትና ይስጥ" ሲልም ጠይቋል።

በማንኛውም የኢትዮጵያ ክልል የንጹሃንን ደም በማፍሰስ፣ በማፈናቀል፣ ሃብትና ንብረታቸውን በመዝረፍና በማውደም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩም ሆነ ድብቅ አጀንዳ የሚያካሂዱ አካላት ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ በማድረግ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

መንግስት ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ቀድሞ በመድረስ የህግ የበላይነትን ማስከበር እንዳለበት የገለጸው መግለጫው፤ ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብና የተጎዱትን ማቋቋም እንዳለበትና ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም