ቀጥታ፡

የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃንን በሕግ በመምራት ለአገር ልማት በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ይደረጋል

ሚያዚያ 12/2013 (ኢዜአ) የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃንን በሕግ በመምራት ለአገር ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንደሚየደረግ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃንና የመገኛ ብዙኃን አገልግሎት የቅሬታና ጥቆማ አቀራረብ፣ ምርመራና ውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ረቂቅ መመሪያን የተመለከተ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን፣ መገናኛ ብዙኃን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ረቂቅ መመሪያው ሲተገበር የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ቴክኖሎጂው የሰጣቸውን ጸጋ ተጠቅመው ለአገር ፓለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ልማት እንዲያውሉ የማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር አቶ መሃመድ ኢድሪስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣውን የቴክኖሎጂ እድገት ተከትሎ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን አማራጭ የመረጃ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን አውስተዋል።

የሳይበር ቴክኖሎጂው በፈጠረው ዕድል የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ተደራሽነት እየሰፋ መሆኑንና ቴክኖሎጂው ድንበር የለሽ ተጽዕኖ የማሳደር ዕድሉ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ስለመሆኑም እንዲሁ።

የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያም በመረጃ የበለጸገ ማኅበረሰብ በመፍጠር ረገድ መልካም ዕድል ይዘው ቢመጡም ዘርፉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም የተዛቡና የተሳሳቱ፤ አብሮነትን የሚሸረሽሩና ጥላቻ አዘል መረጃዎች እንዲስፋፋ አድርጓል ነው ያሉት።

በመሆኑም ዘርፉን በሕግ በመምራት ለፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ልማት መሳሪያ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙኃን የስራ ቡድን ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ጎሹ የመመሪያው ተግባራዊ መሆን በዘርፉ ተገማችና ኃላፊነቱ በግልጽ የሚታወቅ የአስተዳደር ስርዓት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

ረቂቅ መመሪያው ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ሕጎችን በማገናዘብ መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ዶክተር ጸጋ አንዱአለም ናቸው።

በመድረኩ በረቂቅ መመሪያው የተካተቱ ጠንካራ ጎኖችና ውስንነቶች ላይ ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ለመመሪያው ግብዓትነት የሚሆኑ ሃሳቦችም ተወስደዋል።

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ብዙኃን መገናኛ የሕዝብን ሠላምና ደህንነት እንዲሁም ተነጻጻሪ ጥቅሞች ባከበረ መልኩ በኃላፊነት መስራት እንደሚኖርባቸው ይደነግጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም