በከተማዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ

ሚያዚያ 12/2013(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአሽከርካሪ፣ ተሽከርካሪ ፈቃድና እድሳት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የከተማዋ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።
የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ በመተግበሩ የትራፊክ ስርአትን የማክበር ተግባር መሻሻሉንም የከተማዋ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አደም ኑሪ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሽከርካሪ ቦሎ አገልግሎት፣ በመንጃ ፍቃድ እደሳና አዲስ በመስጠት ገቢ ተሰብስቧል።
በዚህም ለ43ሺ ተገልጋዮች አዲስ መንጃ ፍቃድ መሰጠቱንና 263ሺ የቦሎ አገልግሎት ለተሽከርካሪዎች መከናወኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሰጡት አገልግሎቶች ለመሰብሰብ ከታቀደው 1 ነጥብ 19 ቢሊዮን ብር ከእቅድ በላይ በማሳካት 1 ነጥብ 229 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አቶ አደም ጠቅሰዋል።
የገቢ መጠኑ ሊጨምር የቻለው የአገልግሎት ተደራሽነቱ በመስፋቱና በታሪፍ ላይ ቅናሽ በመደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ኢንጂነር ብርሃኑ ግርማ በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ በመተግበሩ የትራፊክ ስርአትን የማክበር ተግባሩ መሻሻሉን ጠቁመው፤ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚከሰተው ሞት ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ቀንሷል ብለዋል።

የትራፊክ ፍሰቱን ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራት አራት አደባባዮችን በማሻሻልና በትራፊክ መብራት የመተካት ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል።
"በተመረጡ የከተማዋ ቦታዎች 20 የእግረኛ ማቋረጫዎችና 2 ነጥበ 5 ኪሎ ሜትር ላይ የመንገድ ዳር መከላከያ ተሰርቷል" ነው ያሉት።
የስነ ምግባር ችግር ባለባቸውና የቅጣት ሪከርድ በተመዘገበባቸው አሽከርካሪዎች ላይ ከሦስት ወር እስከ አንድ አመት የሚደርስ እገዳ መደረጉንም አንስተዋል።
ምክትል ዳይሬክተሩ እንዳሉት በዘጠኝ ወራት ከትራፊክ ቅጣት ከ252 ሚሊዮን 882ሺ ብር በላይ ና ከፓርኪንግ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።
የትራፊክ ደንብ በተላለፉ 1334 የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ጠቅሰዋል።
በከተማዋ ባለቤት አልባ ሆነው የቆዩ 500 ተሽከርካሪዎች በኤጀንሲው መነሳታቸውን ተናግረዋል።