ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል የህግ ማእቀፍ መዘጋጀት አለበት- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል የህግ ማእቀፍ መዘጋጀት አለበት- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 መንግስት ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀት እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ። አመራሮቹ አባሎቻቸው በመሰል ህግ-ወጥ ተግባር እንዳይሳተፉ በየጊዜው ግንዛቤ እንደሚያስጨብጡም አክለዋል። ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈላት በርካታ የምጣኔ ሃብት ምሁራን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተያይዞ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ በቅርቡ ተከስቶ የነበረው መቀዛቀዝ ለአብነት የሚነሳ ጉዳይ ነው። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዜጎች በእጃቸው ያከማቿቸውን የውጭ አገር ገንዘቦች ወደ ባንክ ወስደው እንዲሸጡ ያሳለፉትን ጥሪ ተከትሎ በርካቶች አውንታዊ መለስ ሰጥተዋል። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ደግሞ በህገ-ወጥ መንገድ የውጭ አገር የገንዘብ ኖቶችን ከአገር ሊያሻግሩ ሲሉ በቁጠጥር ስር እንደዋሉ ፖሊስ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። 'ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝወውርን ከዘመቻ ስራ ባለፈ በዘላቂነት መፍታት እንዴት ይቻላል?' ሲል ኢዜአ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አነጋግሯል። የኢትዮጵያ ዴክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫኔ ከበደ ወንጀሉን ለመከከል ብዙም ትኩረት እንዳልተሰጠው ጠቅሰው፤ ጠንከር ያለ የህግ ማዕቀፍ በማውጣት ጥቁር ገበያን መከላከል እንደሚገባ ይገራሉ። የፓርቲው አባላቶች በየጊዜው እየተገናኙ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ላይ እንደሚመክሩ ጠቁመው፤ በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝወውር ሰንሰለት ላይ እጃቸው እንዳይገባም ግንዛቤ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል። የቁጥጥር ስርዓቱ መላላት በአገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ፖለቲዊ ጫና መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ዴክራሲያዊ ህብረት (ኢዴህ) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ ናቸው። የፓርቲያቸው አባላቶች በወንጀሉ እንዳይሳተፉ በህዋስ መዋቅር አማካኝነት ተከታታይ ግንዛቤ እንደሚፈጠርም አክለዋል። መንግስት ጠንከር ያለ ህግ በማውጣትና ተፈጻሚነቱን በመከታተል ወንጀሉን በዘላቂነት ለመከከል መስራት እንዳለበትም ተናግረዋል። የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) ዋና ጸሃፊ ዘመነ ሞላ በበኩላቸው ወንጀሉን በሚመለከት ከመንግስት አካላት ይልቅ ህዝብ ብቻውን እየታገለ መሆኑን ጠቁመው፤ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የአደንዛዥ እጾች እና ህግውጥ የገንዘብ ዝውውር ቢሮ አጠናሁት ብሎ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በዓለም ላይ በዓመት 1 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ዶላር ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ይንቀሳቀሳል። በአህጉር ዓቀፍ ደረጃ በወንጀሉ ስፋት በአደንዛዥ እጾች ምርት የምትታወቀው ደቡብ አሜሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ስትይዝ፤ አህጉረ አፍሪካም ወንጀሉ በፍጥነት እየተስፋፋባት ያለች አህጉር ሆናለች።