ቀጥታ፡

በአፋር ዘግይቶ የተጀመረው የመራጮች ምዝገባ በ1ሺህ 432 ጣቢያዎች እየተካሄደ ነው

ሰመራ፣ ሚያዝያ 12/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ለ6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በ1ሺህ 432 ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአፋር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ጣሃ አሊ ለኢዜአ እንደገለጹት  ዘንድሮ ለሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በተለያዩ ምክንያቶች ከተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ዘግይቶ ተጀምሯል ።

ከጸጥታ፣ ትራንስፖርትና መሰል ችግሮች ጋር ተያይዞ የምርጫ ቁሳቁሶች በወቅቱ ወደ ምርጫ ጣቢዎች መድረስ ባለመቻላቸው የመራጮች ምዝገባ የምርጫ ቦርድ ካስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ዘግይቶ መጀመሩን ተናግረዋል ።

ቦርዱ ከመንግስት ጋር በመተባበር ባደረገው ጥረት በክልሉ በተቋቋሙ በ1ሺህ 432 የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች አስፈላጊው ቅጾች ተሟልተው ካለፈው አርብ ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓም ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ በዘንድሮ ምርጫ ለክልል ምክር ቤት በ32ኛ ለተወካዮች ምክር ቤት በስምንት የምርጫ ክልሎች የተወዳዳሪ ፓርቲዎች እጩዎች መቅረባቸውን ተናግረዋል ።

በሰመራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መዲና አብደላ በሰጡት አሰተያየት በመጪው ግንቦት ለህዝብና ለሀገር የተሻለ ይሰራል ብለው ያመኑበትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ ወስደዋል ።

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይወክለኛል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ ከወዲሁ የመራጭነት ካርድ እንዲወስድ መክረዋል ።

"ይጠቅመኛል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችለኝን ካርድ ወስጃለሁ" ያለው ደግሞ የከተማው ነዋሪ  ወጣት መሀመድ አሊ ነው ።

አሁን ላይ  ዴሞክራሲና ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲሁም ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር የሚሰራ ፓርቲ ለይቶ ለመምረጥ ይቻለው ዘንድ በመገናኛ ብዙሀን የሚተላለፉ የፓርቲዎች የፕሮግራም ትውውቅና የምረጡን ቅሰቀሳዎችን በንቃት እየተከታተለ መሆኑን ተናግሯል ።

 ምርጫዉ ያለምንም ችግር ስላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ወጣት መሀመድ ገልጿል ።

በዘንድሮ ምርጫ ለመወዳደር በክልሉ እየተንቀሳቀሱ ካሉ ሀገራዊ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክና አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ)  እንደሚገኙበት  በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአፋር ቅርንጫፍ ጽህፈት ሀላፊ አቶ ጣሃ አሊ አስታውቀዋል።

እንደ ሀላፊው ገለጻ ከክልላዊ ፓርቲዎች መካከል ደግሞ የአፋር ህዝብ ፓርቲ (አህፓ) እና የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር(አርዱፍ) ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም