ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ያላትን ቁርጠኝነት ለጸጥታው ጥበቃ ም /ቤት አሳወቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ያላትን ቁርጠኝነት ለጸጥታው ጥበቃ ም /ቤት አሳወቀች
ሚያዝያ 11 /2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን ወደ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲመለሱና በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት እንዲያከብሩ ጥሪ ማቅረቧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት እየተካሄደ የሚገኘውን የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በተመለከተ ያላትን አቋም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት በጻፉት ደብዳቤ አስታወቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ም/ቤት አባል አገራት ሱዳን እና ግብጽ በውሃ ሙሌትና አለቃቅ ላይ በማተኮር ወደሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርደር እንዲመለሱ እንዲሁም አገራቱ በአፍሪካ ሕብረት አስባባሪነት የድርድር ሂደትን አንዲያከበሩ ሊያሳስቧቸው ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን ለወቅቱ የተባበሩት የጸጥታ ጥበቃው ም/ቤት ፕሬዚዳንት በፃፉት ደብዳቤ የአፍሪካ ሕብረት ሂደት የተባበሩት መንግስታት መርሆችን እንዲሁም ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህ የታቃኘ በመሆኑ በም/ቤቱ ድጋፍ የተቸረው መሆኑን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጅ ሱዳንና ግብጽ በሁሉም አገራት ተቀባይነት ያለው መፍትሄ ላይ እንዲደረስ በቅን ልቦና እየተደራደሩ እንዳልሆነ በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል።
አያይዘውም አገራቱ ድርድሩን “ማኮላሸት” ምርጫ ማድረጋቸውን እና ጉዳዩን “ዓለም አቀፋዊ ይዘት” በማላበስ ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለመክተት እየሞከሩ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት ለሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ያላትን እምነት እና ቁርጠኝነት አረጋግጠው፣ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም አሁን ደግሞ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርህ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ላደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ያላቸውን ምስጋና ገልፀዋል።
በመጪው ክረምት ከሚካሄደው የሁለተኛው ዙር የግድቡ ሙሌት አስቀድሞ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ኢትዮጵያ ተነሳሽነቱን ወስዳ ላቀረበችው ጥሪ በግብፅና ሱዳን በኩል አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኘች በፃፉት ደብዳቤ አፅዕኖት ሰጥተው ገልፀዋል።
በሁሉን አቀፍ አስገዳጅ ስምምነት ስም ኢ-ፍትሐዊ ሁኔታዎችን በማስጠበቅ እና ኢትዮጵያ በውሃው እንዳትጠቀም ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2015 በሶስቱ አገራት መሪዎች በካርቱም ለተፈረመው የመርሆች ስምምነት ያላትን ቁርጠኛ አቋም ገልጸው፣ ሁለቱ አገራት ግን ከስምምነቱ ባፈነገጠ መልኩ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አቶ ደመቀ በጻፉት ደብዳቤ ጠቅሰዋል።
በመጨረሻም ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለመክተት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ እንዲሁም ድርድሩ ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች በአገራቱ መካከል ያለውን መተማመን አንደሚጎዱ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል።