ቀጥታ፡

ጥፋትን መኮነን ብቻ ሳይሆን መልካም ስራዎችንም የማበረታታት ባሕል ማዳበር ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 በማኅበረሰቡ ውስጥ ግለሰቦችም ሆነ ተቋማትን ጥፋት ሲያጠፋ ከመተቸት በተጨማሪ ለአገርና ወገን መልካም ስራዎችን ያከናወኑ ተቋማትንና ግለሰቦችን የማመስገን ባህል ማዳበር እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። መልካም ለሚሰሩ ምስጋና ማቅረብ ወይም መሸለም ለተመስጋኞች ከሚሰጠው ሞራላዊ እርካታ ባሻገር፤ የጥራት ሽልማት ባሕል በንግዱ ዓለም ተወዳዳሪነትን ለማስፈን አስፈላጊ ተግባር እንደሆነ የሚገልጹም አሉ። ይሁንና በማኅበረሰቡ ውስጥ በብዛት ከምስጋና ይልቅ ወቀሳ ያደላበት ባህል እንዳለ ይገልጻሉ፤ የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ። በግልሰቦች ደረጃ ቢሆንም ራሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ በአካል ተገኝተው ሽልማት የሚሰጡበት የቀድሞው 'የቀዳማይ አጼ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት' ፈር ቀዳጅ ተቋም መሆኑን የሚያስታውሱት አቶ ቴዎድሮስ፣ ነገር ግን እንደሌሎች ተቋማት መንግስት ሲቀየር በመጥፋቱ የሽልማት ባህል አብሮ ሊያደግድ አለመቻሉን ይናገራሉ። "ሰዎችን መሸለም፤ ለሰዎች ሞራል መስጠት ባመጡት ውጤት ላይ የበለጠ እንዲሰሩ የሚያነሳሳ በመሆኑ ሽልማት አስፈላጊ ነው" የሚሉት ደግሞ የቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ መታሰቢያ ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ ሊቀ ካህናት አባይነህ አበበ ናቸው። እናም የሽልማትን ባሕል ማጠናከርና በማህበረሰቡ ውስጥ መልካም ስራ ላከናወኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሽልማት መስጠትና ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ ተግባር መሆኑን አቶ ቴዎድሮስና ሊቀ ካህናት አባይነህ ይናገራሉ። ሰዎች ለሰሩት ስራና ላመጡት ውጤት ሽልማትና ዕውቅና ሲሰጥ እርካታ ሊሰጣቸውና የሰሩት ስራ ዋጋ ማግኘቱን የሚያመላክት መሆን እንዳለበት ሊቀካህናት አባይነህ ጨምረው ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በዋልታ ሚዲያ ትብብር በ2000 ዓ.ም መቋቋሙን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፤ የድርጅቱ ዓላማ የምርትና አገልግሎት ጥራትን በማህበረሰቡ ዘንድ እንደ ባህል እንዲወሰድ ማድረግ ነው። በሉላዊነት ዘመን ጥራት ለወጭና ገቢ ምርቶች አስገዳጅ እየሆነ መምጣቱን ገልጸው፤ በአገሪቱ በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ድርጅቶችን የጥራት ተወዳዳሪነት በመፍጠር ልማትን ማፋጠን የድርጅቱ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የበላይ ጠባቂነት የሚመራው ድርጅቱ እስካሁን ከ250 በላይ ድርጅቶች ከአውሮፓ፣ አሜሪካና ጃፓን በተቀመሩ ሰባት ዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርቶች ተወዳድረው በአምስት ዙር መሸለማቸውን አስታውሰዋል። ከውጭ አገር ወደአገር ውስጥ የሚገቡ ኩባንያዎች ከአገር በቀል ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት በቅድሚያ የሚጠይቁት የጥራት ሰርተፊኬት እንደሆነ በማንሳት፣ የጥራት ሽልማት ባህልን ማዘመን ይጠበቃል ነው ያሉት። በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የሽልማት ድርጅቶች እንሸልማለን በማለት ሽልማትን የመግዛትና መሸጥ አይነት ተግባር እንደሚስተዋል በመግለጽ፤ በሽልማት ላይ እምነት የሚያሳጡ አላስፈላጊ ተግባራትን ለማስወገድ መንግስት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያነሳሉ። ስለሆነም አንድ ወጥ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ያለው የጥራት ሽልማት ተቋም እንደሚያስፈልግ ነው አቶ ቴዎድሮስ ያብራሩት። በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት በርካታ ግለሰቦች ለሽልማት መብቃታቸውን የሚገልጹት ሊቀካህናት አባይነህ፤ እርሳቸው የሚመሩት ማኅበርም ከያዛቸው ዓላማዎች መካከል አንዱ አቅም የሌላቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ነጻ ትምህርት እድል ተጠቃሚ ማድረግና በተለያዩ ስራዎች ውጤታማ የሆኑ ግለሰቦችና ድርጅቶችን መሸለም ነበር። ይሁንና ዓላማውን ለማሳካት በፋይናንስ አቅም እጥረት ሙሉ ለሙሉ ማስኬድ አለመቻሉን ገልጸው፤ ማኅበሩ በቅርቡ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ 126ኛ ልደት በዓል ሲያከብር በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ በርካታ በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። ከነዚህም መካከል አቶ በቀለ ኃይሌ የተባሉ ግለሰብ ለተማሪወች ስኮላርሽፕ ወይም ነጻ የትምህርት ድጋፍ የሚወል አንድ ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል። አባቴ 50 የሚጠጉ ተማሪዎችን በራሳቸው ማስተማራቸውን አስተምረው ማብቃታቸውን የሚገልጹት አቶ በቀለ ኃይሌ፤ ማኅበሩ በትምህርት ላይ የሚሰራውን መልካም ስራ ለመደገፍ የአባታቸውንና ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ለትምህርት የነበራቸውን ጽኑ ፍላጎትና አስተዋጽኦ በመገንዘብ መሆኑን ይናገራሉ። በትምህርት ከፍተኛ ውጤት አምጥተው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን መቀጠል ያልቻሉ ልጆች ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸው በመረዳት ለአገር ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆኑ ማስቻል ነው ያሉት አቶ በቀለ፤ ሌሎች ባለሀብቶችም እኔን ተከትለው እንዲሄዱበት አርዓያ ለመሆን ነው ብለዋል። እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሬ ምን ሰራሁ የሚለውን ማሰብ አለበት የሚሉት አቶ በቀለ፤ መልካም የሚሰሩትን ማመስገንና መሸለም የሚችል ተቋም ማቋቋም ብቻ ሳይሆን ይህን ተቋም የሚረዱ ባለሀብቶችም መኖር እንዳለባቸው አስተያየት ሰጥተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም