ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ልማት ዳያስፖራውን ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ የፖሊሲ ክለሳና የስትራቴጂ ቀረፃ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ልማት ዳያስፖራውን ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ የፖሊሲ ክለሳና የስትራቴጂ ቀረፃ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገለጸ።

በኢትዮጵያ ልማት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እኩል መሳተፍ እንዲችሉ ከግለሰቦች መልካም ፈቃድኝነት ባለፈ በአሰራር የተደገፈ ሰነድ ማዘጋጀት ይገባልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዳያስፖራውን በኢትዮጵያ ልማት ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ በጅማ፣ ወሎ፣ ሀዋሳና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች በጥናት ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ክለሳና የስትራቴጂ ቀረፃ እያከናወነ ይገኛል።

ኤጀንሲው አራቱ ዩኒቨርሲቲዎች በዳያስፖራ ተሳትፎና በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረፃ ለሚያከናውኑት ጥናት መነሻ የሚሆን ጥናታዊ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል::

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ እንዳሉት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ልማት ላይ እስካሁን የሚጠበቅባቸውን ገንቢ አስተዋፅኦ እያደረጉ አይደለም።

በዓለም ዙሪያ ወደ 3 ሚሊዬን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም በሀገራቸው ልማት ላይ የሚሳተፉት ግን አነስተኛ ናቸው።

"አሁን እጃችን ላይ ባለው መረጃ እንኳን በዓለም ላይ ግዙፍ ኢኮኖሚ ማንቀሳቀስ የሚችሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ መለስተኛ ክሊኒክ እንኳን የላቸውም" ብለዋል።

ወጥነት ያለው አሰራር አለመኖር፣ የህግ ክፍተት፣ ቢሮክራሲና ተቀራርቦ አለመስራት ከችግሮቹ መንስኤዎች መካከል መሆናቸውን ገልጸው የሚዘጋጀው የፖሊሲ ክለሳና ስትራቴጂ ቀረፃ እነዚህን ችግሮች የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል::

የሀዋሳ ዪኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር አካለወልድ ፈድሉ፤ ባቀረቡት ትልመ ጥናት እንዳብራሩት በኢትዮጵያ ልማት ላይ ዳያስፖራዎች ያላቸው ተሳትፎ እምብዛም ነው።

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት አራቱ ዩኒቨርሲቲዎች በተሳትፏቸው በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር በፖሊሲና ስትራቴጂ አማራጮች ላይ ሳይንሳዊ ጥናት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መኮንን ቦጋለ በበኩላቸው በውጭ የሚኖሩ አትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ልማት የሚሳተፉበት መንገድ በአሰራር ቢኖርም የተደራጀ አልነበረም ብለዋል።

በመሆኑም ዳያስፖራዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች፤ በቱሪዝም እና ሌሎችም በልማትና የእውቀት ሽግግር ጉልህ አስተዋፆ እንዲኖራቸው ካስፈለገ በግለሰቦች መልካም ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አሰራር መውጣት አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ እድገትና ልማት ተዋናይ ለመሆን ፍላጎት ያላቸው በእኩልነት መሳተፍ የሚችሉት በህግ አግባብ የተቀመጠ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንጂ ነገ በሚያልፉ ቅን ሰዎች ፍላጎት ብቻ መንጠልጠል የለበትም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ፤ የጥናትና ምርምር ተቋማቱ ለሀገራቸው በሚጠቅም መንገድ ከፖለቲካ ነፃ ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ በማሰብ ከመደገፍ ውጭ ምንም አይነት ተሳትፎ የለንም ብለዋል።

የተመራማሪዎችን እውቀት በመገደብ የኛን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ሰነድ እንዲዘጋጅም አንፈልግም፤  ይልቁንስ የምርምር ስራው በጥራት ተከናውኖ በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም