በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 40 ሺ ዶላር ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 40 ሺ ዶላር ድጋፍ አደረጉ
ሚያዚያ 11/2013(ኢዜአ) በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ያሰባሰበውን የ40 ሺ ዶላር ድጋፍ ማስረከቡን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ አስታወቀ።
ኮሚቴው ያሰባሰበውን ድጋፍ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለሚመራው የልዑካን ቡድን፣ ልዩ ልዩ የዳያስፖራ አደረጃጀት አመራሮችና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት መድረክ ነው ያሰረከበው።
የኮሚቴው ሰብሳቢ ቄስ ፍርንሲስ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኮሚቴው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚነዙ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለመመከትና ለግድቡ ግንባታ የሚሆን ሃብት ለማሰባሰብ መመስረቱን ገልጸው፣ እስካሁን ድርስ በመጀመሪያው ዙር ብቻ 40ሺ ዶላር ማሰባሰቡን አስታውቀዋል፡፡
ሁለተኛው ዙር ድጋፍ የማሰባሰብ ሂደትም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ገልጸው፤ ኮሚቴው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃብት ከማሰባሰብ ጎን ለጎን ከልዩ ልዩ አካላት ጋር በመተባባርና የአሜሪካ ምክር ቤት ተመራጮችን በማግባባት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና አድቮኬሲ ስራዎችንም በማከናወን ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በሚኔሶታ የኢፌዴሪ ቆንስል ጀነራል አምባሳደር አብዱላዚዝ መሐመድም በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሃገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ሃብት በማሰባሰብ የሃገር ባለውለታነታቸውን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።በአካባቢው የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በዚህ ሳይወሰኑ በፐብሊክ ዲፕሎማሲና በሃገር ውስጥ የቀጥታ ኢንቨስትመንት እያሳዩ ያለው ተሳትፎም የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እያደረጉ ያለውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የሃብት ማሰባሰብ ድጋፍ ሚሲዮኑ በየጊዜው ከሚያቀርበው ሪፖርት እንደሚከታተሉ አንተስው።
በኮቪድ-19 ምክንያት ዳያስፖራው በችግር ውስጥ ባለበት ሁኔታ እንኳን ሃገሩን ለማገዝ እያደረገ ስላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወ/ሮ ሰላማዊት የኤጀንሲውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያሳይና ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ወቅቱ ዳያስፖራው ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን አጠናክሮ ለሀገሩ መቆምን የሚጠይቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በመነሻ ጽሑፉ ላይ በተወያዩበት ወቅት የዳያስፖራውን ተሳትፎ ተጨማሪ የሃብት ማሰባሰቢያ መንገዶችን በመንደፍ ይበልጥ ማጠናከር ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን አስቀድሞ ማምከንና አጥፊዎችንም ተጠያቂ ለማድረግ ስለተሰሩ ስራዎች እንዲሁም ዳያስፖራው ለሚያከናውናቸው ስራዎች ሰፊ የሚዲያ ሽፋን በመስጠት ሌሎችን ለበለጠ ዓላማ ከማነሳሳት ጋር የተያያዙ ሃሳብና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዳያስፖራው እያደረገ ላለው አበረታች እንቅስቃሴ ምስጋና በማቅረብ፤ ከጊዜያዊ ልዩነት ይልቅ ለሃገራዊ አንድነት መስራቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
የአንዱ አካባቢ ጉዳት የሁሉም አካባቢ ጉዳት እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባና ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት በየአካባቢው ለሚከሰቱ ግጭቶች መነሻ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በሰከነ መልኩ መታየት አለበት ብለዋል።
መንግስት በስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንዳይሰራና ኢትዮጵያ በቀጠናው ጠንካራ ሃገር ሆና እንዳትወጣ ለማድረግ የሚፈልጉ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ሃይል እንዳሉ ግንዝቤ ሊወሰድ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
ዳያስፖራው ነገሮችን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሄዱ የራሱን በጎ አስተዋጽኦ በማበርከት የመንግስትን ጥረት ሊያግዝ እንደሚገባና እስካሁን እያደረጋቸው ያሉ ድጋፎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ ማቅረባቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።