ቀጥታ፡

በኃይማኖት አባቶች መካከል እየተፈጠረ ያለው እርቅ የሀገሪቱን ቀጣይ ሰላም ለማጠናከር ያግዛል - የተለያዩ እምነት ተከታዮች

አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እና እስልምና እምነት ተቋማት ውስጥ እየተፈጠረ ያለው እርቅ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ እምነት ተከታዮች ተናገሩ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ እና አሜሪካ በሚገኙት የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች መካከል የቆየው ቅራኔ ተፈቶ እርቀ ሰላም ወርዷል። በሰሜን አሜሪካ ሲኖሩ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ እና ሌሎች ብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳትም ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ህዝቡን ለማገልገል መወሰናቸው ይታወሳል። ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እና የእምነቱ አባቶች ልዩነቶችን በማስወገድ በአንድነት ሙስሊሙን ለማገልገል የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ማሳወቃቸውም ይታወሳል። በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት እና ድጋፍ በዚህ መንገድ እየተፈጠረ ያለው እርቅ "ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም ነው" ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል። ይህ የተገኘው ሰላማዊ ግንኙነት ዘላቂ እንዲሆን መላው ህዝብ  የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ አሳስበዋል። ወይዘሮ ፍቅር ይበልጣል  የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ባስተያየታቸው" ሲጀመርም ይህ ክፍተት መኖር የለበትም ነበር፤  አሁን ከምንም በላይ ሰላም መሆኑ ተመስገን ነው ለሁላችንም ለኦርቶዶክስ ተከታይ  በተለይ  ቤተክርስቲያኗ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነው ያለው  ˝ብለዋል የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው ወጣት መሃመድ ሻፊ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ወደ መሪነት ከመጡ ጀምሮ በርካታ ትላልቅ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሶ በአንድ ኃይማኖት ውስጥ የሚፈጠርን ቅራኔ በመፍታት ወደ አንድነት እንዲመጡ ያደረጉትን ጥረት አድንቋል። ታዳጊ አልአዛር ሰለሞን የአባቶች መታረቅና ወደ አንድነት መምጣት ቤተክርስቲያኗ እንድትጸና አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግሯል። በሰሜን አሜሪካ ሲኖሩ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ እና ሌሎች ብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት ነገ ወደ ሀገር ቤት ይመለሳሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ቤተክርስቲያኗም ደማቅ አቀባበል ለማድረግ እየተዘጋጀች መሆኗን አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም