በአፍሪካ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር 118 ሺህ እየተጠጋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር 118 ሺህ እየተጠጋ ነው
ሚያዚያ 11/2013 (ኢዜአ) በአፍሪካ አህጉር በኮሮና ቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 118 ሺህ እየተጠጋ ነው። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ማሻቀቡ ተነግሯል።
ኦል አፍሪካን ዶት ኮም እንዳስነበበው በአህጉሩ 55 አገራት የቫይረሱን መገኘት ሪፖርት አድርገዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ሲሆን ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥርም ከ117 ሺህ 800 በላይ ደርሷል ብሏል።
ወረርሽኙን ለመከላከልም ከ9 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የኮቪድ-19 ክትባት በአህጉሩ መሰራጨቱን ዘግቧል።
በቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጠቁት መካከል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ሪፖርት በማድረግና ከ53 ሺህ በላይ ዜጎቿን በሞት በማጣት ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን ሞሮኮ፣ ቱኒዚያና ኢትዮጵያ ይከተላሉ።
በኢትዮጵያ ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር ከ242 ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ መጠን እየተስፋፋ እንደሆነም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
በየዕለቱ ወደ ጽኑ ሕሙማን ሕክምና ክፍል የሚገቡና የመተንፈሻ መሳሪያ የሚያስፈልጋቸው እገዛውን ባለማግኘታቸው ሕይወታቸውን እያጡ ያሉ ሰዎች ቁጥርም እያሻቀበ ነው።
በመሆኑም ማስክ፣ ሳኒታይዘር፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ሕዝብ የሚበዛባቸውን ቦታዎች አለማዘውተርና ሌሎች የጥንቃቄ መንገዶችን በትክክል መተግበር እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ከአንድ ዓመት በፊት በቻይና በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከ142 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መያዛቸው ሲረጋገጥ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።