በአማራ ክልል በ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ
ባህርዳር ሚያዝያ 10/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ዘንድሮ በተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ 153 ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተላቸው።
የክልሉ ዕርሰ መስተዳድር አቶ አገኘው ተሻገር በተገኙበት ዛሬ በባህርዳር ለተማሪዎቹ የተበረከተው የገንዘብና የላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ሽልማት ከመንግስትና ከባለሀብቶች በተገኘ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የተሸፈነ መሆኑን በስነ ስርአቱ ላይ ተመላክቷል።
የክልሉ ዕርሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በወቅቱ እንደተናገሩት ተማሪዎች ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተከባብሮና ተባብሮ ለመኖር የሚያስችሉ እሴቶችን በማጎልበትና ከዘረኝነትንና ጎጠኝነት አስተሳሰብ በመራቅ ለክልሉና ለሀገሪቱ ሀሌንታ ለመሆን መትጋት ይገባቸዋል።
ትምህርት ግለሰባዊ አመለካከትን ከመገንባት ባለፈ ሀገር በተሻለ ልማት ወደፊት እንድትጓዝ የሚያደርግ አይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
“የክልሉ መንግስት ተማሪዎች በገንዘብ እጥረት መክንያት መድረስ ካለባቸው ደረጃ እንዳይ ደናቀፍ ለማድረግ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል
ሽልማቱ መሰረተ ልማት ባልተሟላባቸው ትምህርት ቤቶች በመማርና የኮቪድ -19 ተግዳሮቶችን ተቋቁመው ለውጤት የበቁ ተማሪዎችን ለማበረታታት ያለመ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ናቸው።
ከመንግስትና ከባለሀብቶች በተገኘ ገንዘብ ለተማሪዎቹ በነፍስ ወከፍ ከ18 ሺህ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብና ላፕቶፕ ኮምፒውተር በሽልማት የተበረከተላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ በፈተና ውስጥ በማለፍ ለውጤት መብቃት እንደሚቻል ለተከታዮቻቸው አርአያ መሆን እንደቻሉ የገለጹት ዶክተር ይልቃል “ተማሪዎቹ ለችግሮች ሰበብ ከመፈለግ ይልቅ ችግሮችን በእራስ አቅም መፍታት እንደሚቻል ያሳዩ ናቸው” ብለዋል።
ተማሪዎቹ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ያስመዘገቡትን ውጤት እስከ መጨረሻው የትምህርት ሕይወታቸው ፈተናዎችን በመጋፈጥ እንዲያስቀጥሉ አስገንዘበዋል።
በክልሉ ዘንድሮ በተሰጠው የ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከተቀመጡ 78ሺህ 800 ተማሪዎች መካከል 66 ነጥብ 1 በመቶዎቹ 350ና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸውን ዶክተር ይልቃል አስታውቀዋል።
በክልሉ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከቋሪት ከፍተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት አንደኛ የወጣው ተማሪ አእምሮ ደመመው “የክልሉ መንግስት ለውጤታማ ተማሪዎች የገንዘብና የትምህርት ቁሳቁስ ሽልማት ማዘጋጀቱ ለበለጠ ውጤት የሚያነሳሳ ነው” ብሏል።
ሽልማቱ በቀጣይም በዩኒቨርስቲ ቆይታው የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሞራል ስንቅ እንደሚሆነው ገልጿል።
የክልሉ መንግስት ለውጤታማ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት መሰጠቱ ተከታይ ተማሪዎችን ለበመጠ ትጋት ያነሳሳል” ያለችው ደግሞ ከሰሜን ዕዝ መርሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 621 ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪ ሊያ ወርቁ ናት።
በስነ-ስርአቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የተማሪ ቤተሰቦችና ተሸላሚ ተማሪዎች ተገኝተዋል።