በመተከል ዞን ማረሚያ ቤት የነበሩ 124 የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ ተለቀቁ

78

ሚያዚያ 9/2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማረሚያ ቤት የነበሩ 124 የሕግ ታራሚዎች ዛሬ በይቅርታ ተለቀቁ፤ ከእነዚህ መካከል ሦስቱ ሴቶች ናቸው።

ከእስር የተለቀቁት ታራሚዎች በበኩላቸው በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ባገኙት ሙያ ሰርተው ለመለወጥ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

የመተከል ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ዳምጤ ሊዴ የክልሉ የይቅርታ ቦርድ በ2013 ሦስተኛ ሩብ ዓመት የአንድ ሦስተኛ መመሪያ በማውጣት መስፈርቱን የሚያሟሉ 304 የሕግ ታራሚዎች እንዲፈቱ ወስኗል።

ከእነዚህ መካከል124ቱ በመተከል ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ግልገል በለስ እስር ቤት የነበሩ ናቸው።

ታራሚዎቹ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ፈፅመው የተፈረደባቸውና የእስር ጊዜያቸውን ሲሶ የጨረሱ፣ መልካም ስነ ምግባር ያላቸውና ኅብረተሰቡን ቢቀላቀሉ ማስተማር ይችላሉ ተብለው የታመነባቸው እንደሆኑም ገልፀዋል።

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች የዞኑ አመራሮችና የኮማንድ ፖስት አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ተለቀዋል።

የመከላከያ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እና የምዕራብ ዕዝ ዘመቻ ኃላፊ ኮሎኔል ፋሲል ይግዛው የሕግ ታራሚዎቹ ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሌሎችን ማስተማር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ወጣቶች የልማት ኃይል በመሆን አምራች ዜጋና የሠላም አምባሳደር ሊሆኑ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በመተከል ዞን ዜጎችን እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚፈልጉ የስልጣን ጥመኞች መኖራቸውን ጠቁመው፤ የተለቀቁት ታራሚዎች ለም በሆነው አካባቢያቸው ሰርተው መለወጥ እንጂ ለከፋፋይ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እንዳይሆኑም አሳስበዋል።

የፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዘሪሁን ወርቁ በበኩላቸው ታራሚዎች ከእስር ሲወጡ ዳግም ወንጀል ውስጥ መግባትና መሳሳት እንደሌለባቸው ይልቁኑም ከፀጥታ አካላት ጎን ለሠላም መቆም እንዳለባቸው መክረዋል።

ኮሎኔል ጌትነት፣ ኮሎኔል ፋሲል እና ኮማንደር ዘሪሁን፡-

በይቅርታ ከእስር የተፈቱት ታራሚዎች በበኩላቸው በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ባገኙት ሙያ ሰርተው ለመለወጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ታራሚዎቹ እንዳሉት በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የተለያዩ የዕደ ጥበብና ሽመና ሙያዎችን ቀስመዋል። 

ታደሰ ያሰብ፣ ሀፄ መጃኔ እና መንግስቱ ጉስዋሮ በፈፀሙት ወንጀል ለዓመታት በማረሚያ ቤት መቆየታቸውንና በቆይታቸውም የሙያ ባለቤት መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ሕይወት በእስር ቤት መራራ ብትሆንም በእስር ቤት ውስጥ በሚሰሩት ስራ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን ሲደግፉ መቆየታቸውንና በይቅርታ በመፈታታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል። 

ወንጀል በመፈጸማቸው መጸጸታቸውን የገለጹት ታራሚዎቹ ሌሎች ሰዎች ወንጀል ፈፅመው ሕይወታቸውን ለእስር እንዳይዳርጉ መክረዋል። 

 ወደ ኅብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ባገኙት ሙያ ኑሯቸውን መምራት እንደሚሹም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም