ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በልዩነት ውስጥ ብዝሃነትን፤ በብዝሃነት ውስጥ ልዩነትን የሚቀበል ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል

ሚያዚያ 09/2013 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ በልዩነት ውስጥ ብዝሃነትን፤ በብዝሃነት ውስጥ ልዩነትን አምኖ የሚቀበልና በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ማንነትን የሚያከብር ስርዓት መገንባት እንደሚያስፈለግ ተመላከተ።

ኢትዮጵያ ራሷን ለማሸጋገር ያገኘቻቸውን እድሎች አለመጠቀሟና ብሔር ተኮር ፖለቲካ ለቀውሶች ተጋላጭ እንዳደረጋትም ተገልጿል።

መቀመጫው አሜሪካ የሆነው "ኢትዮጵያዊነት" ዓለም አቀፍ የሲቪክ ተቋም "በኢትዮጵያ አሁን ላሉ ቀውሶች የምዕራባዊያን ምላሽ የሚኖረው ውጤት" በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የበይነ መረብ መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የኢትዮጵያና የውጭ አገራት ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ፖለቲከኞች እየተሳተፉ ነው።

የታሪክ ምሁርና የፖለቲካ ተንታኝ ልዑል አስፋወሰን አስራት ኢትዮጵያ በታሪክ ለተለያዩ ቀውሶች ተጋላጭ ከሆነችባቸው ምክንያቶች አብዛኞቹ ከውስጣዊ ጉዳዮች የመነጩ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ የመንግስት ስርዓቶች ውስጥ በነበሯት ሽግግሮች የመንግስት አወቃቀር ስርዓቷን ለማስተካከልና ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት ያገኘቻቸውን ታሪካዊ አጋጣሚዎች እንዳልተጠቀመችባቸው ገልጸዋል።

በተለይም ጠንካራ የመንግስት ስርዓት አለመገንባቷ በየጊዜው ለሚፈጠሩ ቀውሶች ተጋላጭ እንድትሆን ማድረጉን አመልክተዋል።

የሰለጠነና በምክንያታዊነት የሚያምን ማኅበረሰብ አለመፈጠሩ ግጭቶች እንዲፈጠሩና በዜጎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት መሆኑንም ነው ልዑል አስፋወሰን ያስረዱት።

ህወሓት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ዜጎች በብሔር ማንነታቸው እንዲከፋፈሉ ሲያራምደው የነበረው የብሔር ፖለቲካ ውጤቱ አሁን እየታየ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት እየተገደሉና እየተፈናቀሉ እንደሆነም አንስተዋል።

ብሔር ላይ መሰረት ያደረገው ማንነት ግጭቶችን በመፍጠር ኢትዮጵያን ለቀውስ እየዳረጋት መሆኑንም ገልጸዋል።

በስራ ላይ ያለው ሕገ-መንግስትም ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ሳይሆን ዜጎች በብሔራቸው ጥላ ስር እንዲጠለሉ አድርጓቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ለዘመናት የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ሃይሎች በተለያየ መልኩ ሲፈጽሙት የነበረው ተግባር ኢትዮጵያን ለቀውስ እንድትጋለጥ ማድረጉን አውስተዋል።

አሁን ላለው ችግር መፍትሔው በልዩነት ውስጥ ብዝሃነትን፤ በብዝሃነት ውስጥ ልዩነትን አምኖ የሚቀበል እንዲሁም በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ማንነትን የሚያከብር ስርዓት መገንባት ነው ብለዋል ልዑል አስፋወሰን።

በኢትዮጵያ የአገረ መንግስት ግንባታው ኢትዮጵያዊነትን መሰረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባና አዲስ ሕገ መንግስት ሊዘጋጅ እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ሕዝብ የሚያምነውና የሚቀበለው እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

ዜጎችን ማዕከል ያደረገ የኢኮኖሚ እድገትና ለውጥ ለሚነሱ ቀውሶች መፍትሔ ለማበጀት ቁልፍ መሆኑንም አክለዋል።

መንግስትም እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎችና ግጭቶችን በማስቆም የሕዝቡን ሠላምና ደህንነት የማረረጋገጥ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዓለም አቀፍ የሲቪክ ተቋም "ኢትዮጵያዊነት" ሊቀመንበር ዶክተር እርቁ ይመር በበኩላቸው ዜጎችን በዘርና በብሔር ለመከፋፈል የተሰራው ስራ የኢትዮጵያዊነት ማንነትና እሴቶች እንዲሸረሸሩ አድርጓል ብለዋል።

በመሆኑም አሁን በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ዋነኛው መፍትሔ ኢትዮጵያዊነትን እንደገና መገንባትና ዜጎችም የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዲላበሱ ማድረግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አገራቸው የተጋረጡባትን ፈተናዎች በጋራ መመከት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

በበይነ መረብ መድረኩ ለውይይት በተዘጋጁ የተለያዩ ርዕሶች ምሁራን ገለጻ እያደረጉ ሲሆን ገለጻውን ተከትሎ ለሚነሱ ሀሳቦችና ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ የኢትዮጵያዊነት የሲቪክ ተቋም የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የማጠቃለያ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም