የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ክትባት ወደ ብራዚል ሳኦ ፖሎ አጓጓዘ

70

ሚያዚያ 9 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአፍሪካ ግንባር ቀደም አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ክትባት ከሻንጋይ ወደ ብራዚል ሳኦ ፖሎ አጓጉዟል፡፡

የኢትዮጵያ ካርጎ እና ሎጅስቲክስ አገልግሎቶች እስካሁን ከ 20 ሚሊዮን በላይ ክትባቶችን ከ 20 በላይ ወደሚሆኑ አገሮች አጓጉዟል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም እንደገለፁት፤ አየር መንገዱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የሚደረገውን የመከላከል ጥረት ለማገዝ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡

"ወረርሽኙን ለመታገል እና ህይወትን ለማዳን ያለን ቁርጠኝነት በአፍሪካም ሆነ ከዚያ ባሻገር የማይናወጥ ሆኖ ቆይቷል" ብለዋል፡፡

ክትባቱን አጓጉዞ በወቅቱ ማድረስ መቻል ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠር የሰው ልጅን ህይወት ከሞት መታደግ እንደሆነ ገልጸው፤ “በዘመናዊ መሠረተ ልማት እና በትጉ ሠራተኞች ጥረት ክትባቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማጓጓዝ ላይ እንገኛለን” ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ ከአፍሪካ ባሻገር መድረስ በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ ወረርሽኙን ለመመከት በሚደረገው ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በክትባት ስርጭቱ አየር መንገዱ እንደሚሰራ መናገራቸው የአሜሪካ ጆርናል ኦፍ ትራንስፖርቴሽን ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ እቃ ጫኝነት በመቀየር የጭነት አቅሙን ያሳደገ ሲሆን በሚሰጠው ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም