ቀጥታ፡

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ለተፈናቃዮች መጠለያ ግንባታ የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ሚያዚያ 8 /2013 (ኢዜአ) የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ለተፈናቃዮች የመጠለያ ግንባታ የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምሳደር ጊታ ፓሲ ለዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሞሪን አቼንግ አስረክበዋል።

የተደረገው ድጋፍ 1 ሺህ 500 የፕላስቲክ ንጣፍ ሲሆን በትግራይ ክልል ከመኖሪያ ቤታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች መጠለያ ለመስራት የሚያገለግል እንደሆነ ተገልጿል።

ከመጠለያ ቁሳቁስ በተጨማሪም ምንጣፍ፣ ብርድ ልብስ እና መሰረታዊ የቤት ዕቃዎች በድጋፉ ተካተዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ የፕላስቲክ ንጣፉ በትግራይ ክልል ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ በ10 ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች አስቸኳይ መጠለያ ለመስራት የሚያገለግል እንደሆነ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት እስኪቋቋሙ የአሜሪካ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አምባሳደሯ አረጋግጠዋል።

የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሞሪን አቼንግ በበኩላቸው የቁሳቁስ ድጋፉ ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት የኑሮ ሁኔታ እስከሚመለሱ ድረስ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ድጋፉ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ትግራይ ክልል እንደሚላክም አረጋግጠዋል።

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ያሲን ነሲቡ በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም