ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ መብቱን በመጠቀም የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያበቃውን ካርድ መውሰድ እንዳለበት ተመለከተ

ሆሳዕና/አርባምንጭ ፤ሚያዚያ 8/2013(ኢዜአ) ህብረተሰቡ መብቱን በመጠቀም የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያበቃውን ካርድ ከወዲሁ ተመዝግቦ መውሰድ እንዳለበት ተመለከተ።

ብልጽግና እና እናት ፓርቲዎች  በሆሳዕና እና አርባምንጭ ከተሞች   የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በሆሳዕና ከተማ የምርጡኝ ቅስቀሳ ባካሄደበት ወቅት የፓርቲው ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ርዕዮተ አለም ግንባታ ዘርፍ  የሆሳዕና ኃላፊ አቶ ጸጋው ሙሉጌታ እንዳመለከቱት፤  ህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ ከወዲሁ የመራጭነት ካርድ መውሰድ ይኖርበታል።

ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ መጻኢ እድልን የተሳካ እንዲሆን ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።

ህብረተሰቡ መብቱን ተጠቅሞ የሀገሪቱን እድገት ሊያሳካ የሚችል ፓርቲ በመምረጥ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በቅስቀሳው ድጋፋቸውን ለመግለጽ የተገኙት የሆሳዕና ከተማ ሜል አምባ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እመቤት አባ በሰጡት አስተያየት መብታቸውን በመጠቀም ለሀገሪቱ ልማት፣ ሰላምና የዜጎች እኩል ተጠቃሚነት ለማምጣት የሚሰራ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም ብቁ ለመሆን  ተመዝግበው የመራጭነት ካርድ በእጃቸው እንዳስገቡና ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ከሌሞ ወረዳ አምብቾ ጎዴ ቀበሌ የተገኙት አቶ በቀለ ፎርሲዶ በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን የሚያስቀጥልና ከምንም በላይ ለሰላም ዋጋ የሚሰጥ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ወጣት ተመስገን ዮሀንስ በበኩሉ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ  እንዲጠናቀቅ ወጣቱ ከማንም በላይ ትልቅ ሀላፊነት እንዳለበትና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግሯል።

ለመራጭነትም ተመዝግቦ ካርድ እንደወሰደም ገልጿል።

በተመሳሳይ እናት ፓርቲ በአርባምንጭ ባካሄደው የጎዳና ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ፓርቲው የጋሞ ዞን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ መምህር ሀብተሚካኤል ቃይዳ እንደገለጹት ፤ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለማሸነፍ ቅስቀሳና ማንፌስቷቸውን የማስተዋወቅ ስራ እያካሄዱ ነው።

አሁን ያለው የሀገሪቱ ህገ-መንግስት የአንድ ፓርቲ ፍላጎት ማንጸባረቂያ በመሆኑ አብዛኛው ዜጋ ተጠቃሚ አልሆነም ያሉት አስተባባሪው ፓርቲው ቢመረጥ በእናታዊ እሳቤ ማዕቀፍ መላውን ህዝብ ያማከለ ህገ-መንግስት ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የትምህርት ፖሊሲውም ቢሆን ከምዕራባዊያን የተቀዳና ሀገር በቀል ዕውቀትን የዘነጋ በመሆኑ ፓርቲው ቢመረጥ ለባህላዊ እሴቶችና ህብረተሰባዊ ዕውቀቶች ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በስነ-ምግባር የታነጸና ሀገር ወዳድ ዜጋ ለመፍጠር እንሰራለን በለዋል።

እስካሁን በምርጫ እንቅስቃሴው ፓርቲው ያጋጠመው ችግር ባይኖርም በማይታወቁ አካላት የምርጫ ቅስቀሳ ባነሮች ከተለጠፉበት እየተገነጠሉ እየጠፉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፓርቲው በጋሞ ዞን ለህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች አስር  ዕጩዎችን አቅርቧል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም