ቀጥታ፡

በሀገሪቱ ትላልቅ ካምፓኒዎች ወደ ማዕድን ልማት ዘርፎች መግባት ጀምረዋል-ኢንጂነር ታከለ ኡማ

አሶሳ፣ ሚያዚያ 08 / 2013( ኢዜአ )  በሀገሪቱ ትላልቅ ካምፓኒዎች ወደ ወርቅ እና ሌሎች የማዕድን ልማት ዘርፎች መግባት መጀመራቸውን የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ወረዳ በዓመት ሰባት ኩንታል ወርቅ ማምረት የሚያስችል ኩባንያ ወደ ምርት ለማስገባት ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

ሚኒስትሩ  በወቅቱ እንዳሉት፤  ወርቅ ማምረት እና መጠቀም ከሃገሪቱ  ታሪክ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው፡፡

በተለይ ከሃገራዊ ለውጡ በፊት በዘርፉ የፖሊሲ እጦት እና የአሰራር ማነቆዎች ዋነኛ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸውን  አስታውሰዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታት የረጅም ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን የተናገሩት  ኢንጂኒየር ታከለ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ህግ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ትላልቅ ካምፓኒዎች በወርቅ እና ሌሎች የሃገሪቱ ማዕድን ዘርፎች መግባት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

ለዚህም ዛሬ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለትን የኩርሙክ አላይድ ጎልድ ኮርፕ ካምፓኒን ጠቅሰዋል ፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ አንጡራ ህብት የሆነውን ማዕድን ለረጅም ዓመታት ይዘው ሳያለሙ ያስቀመጡ በርካታ ባለሃብቶች መኖራቸውን ኢንጂነር ታከለ ጠቁመዋል፡፡

ይህም ህብረተቡም ከሃብቱ እንዳይጠቀም ማድረጉንና ወጣቱም ተደራጅቶ እንዳያለማ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል፡፡

ችግሩ በአብዛኞቹ የሃገሪቱ አካባቢዎች እንደሚታይ አመልክተዋል፡፡

መንግስት ከእነኚህ ባለሃብቶች ላይ በህጋዊ መንገድ ሃብቱን በመረከብ እውነተኛ አልሚ ባለሃብቶች የማስተላለፍ እርምጃ ለመውሰድ በጥናት ላይ የተሞረከዘ ዝግጅት አጠናቋል ብለዋል፡፡

ዓላማው የተፈጥሮ ሃብቷን አልምታ ዜጎቿን እኩል የምትጠቅም ሃገር መገንባት ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ ለዚህ ደግሞ የተፈጥሮ ሃብትን በፍትሃዊነት እና ሃላፈነት በተሞላው መንገድ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግስት ለወርቅ ልማት በሰጠው ትኩረት ተደራጅተው የሚያመርቱ ወጣቶች ማህበራት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ በባህላዊ መንገድ የተመረተ 15 ኩንታል ወርቅ ከክልሉ ወደ ብሄራዊ ባንክ ገብቷል ብለዋል፡፡

ዛሬ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ካምፓኒ ማምረት ሲጀምር የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያሳደገው ገልጸዋል፡፡

ካምፓኒው የአካባቢ ጥበቃን ስራን ጨምሮ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች  ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል፡፡

የወርቅ ሃብት በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች እንደሚገኝ ያመለከቱት አቶ አሻድሊ ሌሎች ባለሃብቶች ከካምፓኒው ተሞክሮ በመውሰድ በዘርፉ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአላይድ ጎልድ ካምፓኒ ስራ አስኪያጅ አቶ ብሮክስ ውርቁ  ካምፓኒው ሁለት ቢሊዮን ብር በመመደብ ባደረገው ጥናት 72 ሺህ ኪሎ ግራም ሪዘርብ ወርቅ አግኝቷል ብለዋል፡፡

ካፓኒው ከ18 ወራት በኋላ ማምረት እንደሚጀምር ገልጸው በዓመት ከሰባት ኩንታል በላይ ወርቅ የማምረት አቅም እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

ለፋብሪካው ግንባታ ካምፓኒው 14 ቢሊዮን ብር እንደመደበ አስታውቀዋል፡፡

ካምፓኒው በአፍሪካ ካሉ ወርቅ አምራች ካምፓኒዎች ጋር ተወዳዳሪ እንደሆነ አመልክተው ይህም ትላልቅ የዓለም አቀፍ ካፓኒዎችን ወደ ሃገር ውስጥ መሳብ እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

እያንዳንዷ ቀን ተስፋችን ናት ያሉት አቶ ብሮክስ ፋብሪካው ለኢትዮጵያ ተስፋ ይዞ ይመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም