ቀጥታ፡

በሀድያ ዞን የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መሰረቱ

ሆሳዕና፤ ሚያዚያ 08/2013(ኢዜአ) በሀድያ ዞን የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመነጋገር ለመፍታት የሚያስችላቸውን የጋራ ምክር ቤት መሰረቱ።

የጋራ ምክር ቤቱን ከመሰረቱት  መካከል ብልጽግና ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ/ኢሶዶፓ/፣ እናት ፓርቲ እና  የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ/መኢአድ/ ይገኙበታል።

የጋራ ምክር ቤቱ  የመኢአድ  ሊቀ መንበር  አቶ ጌታሁን ኑራሞን በዋና ሰብሳቢነት ፣ የኢሶዴፓ ሊቀመንበር አቶ አጫሞ ቦቄን በምክትል ሰብሳቢነት የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የሀድያ ኃላፊ አቶ ሲሳይ እውነቱ ደግሞ በጸሀፊነት መርጧል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ በወቅቱ እንዳሉት፤ በምርጫው ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመነጋገር ለመፍታትና ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ የምክር ቤቱ መቋቋም ትልቅ ፋይዳ አለው።

ከምርጫ ጋር ተያይዞ  አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በፍጥነት ለማስተካከል  እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና  ታዕማኒ እንዲሆን በማድረግም የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ከብልጽግና ጋር አብሮ በመስራት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ በበኩላቸው ፤ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በእጩዎችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በቅርበት ለመፍታት የጋራ ምክር ቤቱ መቋቋም አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የምክር ቤቱ ጸሀፊ ናቸው።

የጋራ ምክር ቤቱን የመሰረቱት ፓርቲዎች የመተዳደሪያ ደንብ በማርቀቅ በቅርቡ እንደሚያጸድቁ የሚጠበቅ መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም