በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተከሰሰው ግለሰብ በ16 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት

118

ፍቼ ፣ሚያዚያ ዐ8/2013(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተከሰሰው ግለሰብን በ16 ዓመት እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን አስታወቀ።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ቅጣቱን ያሳለፈው በዞኑ  ደራ ወረዳ ጉንዶ መስቀል ከተማ ነዋሪ በሆነው አበራ በየነ በተባለው ግለሰብ ላይ ነው።

የእስራት ቅጣቱ የተወሰነበት ግለሰብ ገንዘብ ለማግኘት ሲል ግንቦት 21/2012 ዓ.ም 16 ወጣቶችን ወደ ሱዳን ድንበር አካባቢ ወስዶ ለከፋ ጉዳትና እንግልት መዳረጉን በአቃቤ ሕግ የጽሁፍና የሰው ማስረጃ ተረጋግጦበት መሆኑን የችሎቱ የመሀል ዳኛ አቶ ሽመልስ ግርማ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ግለሰቡ ወጣቶቹን ሱዳንና ሊቢያ እልካችኋለሁ ብሎ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላም በመሰወር በአዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች ሲዘዋወር ቆይቶ መያዙን ያወሱት ዳኛው  በዚህም ጥፋት እስከ 20 ዓመት ሊደርስ በሚችል እስራትና ገንዘብ የሚያስቀጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ግለሰቡ ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ ስለሌለው ቅጣቱ እንደቀለለት አስረድተዋል፡፡

ጥፋተኛ የተባለው ግለሰብ የፈፀመውን የወንጀል ክስ ሊያስተባብልና ሊከላከል ባለመቻሉ ቅጣቱ እንደፀናበትና ይግባኝ የማለት መብቱንም ፍርድ ቤቱ የፈቀደ መሆኑን  አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም