ግብፅ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያላት ብቸኛ አማራጭ መደራደር ነው-አለም አቀፍ ምሁር - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያላት ብቸኛ አማራጭ መደራደር ነው-አለም አቀፍ ምሁር
ሚያዚያ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) ግብጽ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ አሁን ባለበት ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋር በቀና መንፈስ ከመደራደር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት ጂ ኦ ፖሊቲካል ፊውቸር በተባለ የአሜሪካ የጥናት ተቋም ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ሂላል ክሃሻን ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እየተገነባ ያለው በኢትዮጵያ መብራት ለማያገኘው ከ60 በመቶ በላይ ለሚሆነው ህዝብ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ መሆኑን ተመራማሪው ጠቁመዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያውን ያላቸውን ሁሉ የከፈሉበት ግንባታ መሆኑን ያብራሩት ምሁሩ ግድቡ ተጠናቅቆ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር ከሚያመነጨው 6ሺህ 500 ሜጋ ዋት ውስጥ የተወሰነው ለጎረቤት ሃገራት የሚላክ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ባለፈው ሃምሌ ወር ግድቡ 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ እንዲይዝ ሲደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ልማት የማይቀለበስበት ደረጃ መድረሱን ማሳያ ነው ማለታቸውን ያስታወሱት ምሁሩ ግድቡ በመጪው ክረምት 13 ነጥብ 5 ቢሊየን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ እንደሚይዝ ይጠበቃል ብለዋል።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ በ1929 እና በ1959 ስምምነቶች የአንበሳውን ድርሻ ስትወስድ ለነበረችውና “ታሪካዊ መብቴ ይጠበቅልኝ” ለምትለው ግብጽ ይሄ ሃቅ ሊዋጥላት አለመቻሉን ጠቁመው የህዳሴው ግድብ ይህንን ታሪክ ሊቀይረው ይችላል የሚል ስጋት እንደገባት ገልጸዋል።
ግብጽ ታሪካዊ መብቴ የምትለው አቋም ኢትዮጵያውያንን እና የግድቡን ግንባታ የሚደግፉ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ያስቆጣ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
በዚህ ምክንያት ግብጽ አሁን ላይ ተስፋዋ እየተሟጠጠ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የመርህ ስምምነቶች ላይ ማተኮር የመረጠችው ግብጽ “55 ቢሊየን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ እንዲሁም በድርቅ ወቅት ሊፈጠር ለሚችለው የውሃ እጥረት ዋስትና ይሰጠኝ” በማለቷ እንደሆነ ያብራሩት ተመራማሪው በሚቀጥለው ሃምሌ ስለሚጀመረው የውሃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን ለመረጃ ልውውጥ ባለሙያዎቻቸውን እንዲልኩ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ሃሳብ ጊዜ ማራዘሚያ ነው በማለት ሳይቀበሉት መቅረታቸውን አስታውሰዋል።
የግብጹ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለላይኞቹ የአባይ ተፋሰስ ሃገራት ወንዙን የማልማት መብት ይሰጣል በሚል እ.ኤ.አ በ2015 የተደረሰውን የመርህ ስምምነት መፈረም እንዳልነበረባቸው የሚወተውቷቸው አካላት እንደነበሩም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ድርድሩን በሚመለከት የትኛውንም የውጭ ሃይል ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል እየታወቀ የግብጽ ብቸኛው አማራጭ ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መደራደር እንደሆነ ምሁሩ መክረዋል።
አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ የማይቆምበት ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ያመለከቱት ተመራማሪው ከአጼ ሃይለስላሴ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ድረስ ለውይይት ያላቸውን ፍላጎት በመገንዘብ አል ሲ ሲ ከቀድሞ ጀምሮ የግብጽ መሪዎች የሰሩትን ስህተት ለማረም መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።