የኢትዮጵያ እና ቼክ የንግድ ግንኙነት ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ቼክ የንግድ ግንኙነት ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 በኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ ከሚፈለገው በታች መሆኑን የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ገለጸ። ለዚህ ደግሞ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች በትክክል ተግባራዊ ስለመሆናቸው ቁጥጥር ባለመደረጉ ነው ብሏል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰት ለማቀላጠፍ የኢትዮ-ቼክ ሪፐብሊክ የቢዝነስ ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በቼክ ሪፐብሊክ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ሚኒስትር የሚመራ የልዑካን ቡድን ከአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል። የሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1930ዎቹ ነው። ይሁን እንጂ ግንኙነቱ በወታደራዊ፣ ግብርናና ጤና ዘርፎች ቢሰፋም የንግድና ኢንቨስትመንት መጠኑ የሚፈለገውን ያህል መሆን አልቻለም ይላሉ የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤሊያስ ገነቲ። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2012 እስከ 2017 በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው የንግድ መጠን 118 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ድርሻ 18 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች ቡናና አደንጓሬ ከመሆኑም ባለፈ በተለያየ ጊዜ የተፈራረመቻቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች በትክክል ባለመተግበራቸው ነው ብለዋል። ሁለቱ አገሮች እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2007 ተደራራቢ ታክስን የሚያስቀርና የታክስ ስወራን የሚከላከል ስምምነት ቢፈራረሙም ለውጥ ማምጣት አልቻሉም ነው ያሉት። የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና የቼክ ሪፐብሊክ የንግድ ምክር ቤት የሁለቱን አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ "ድጋፍ ለንግድ" የሚል ስምምነት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2016 ተፈራርመዋል። በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ የሁለቱን አገሮች የግል ባለሃብቶች ለማነሳሳት ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ ለማጣጣም የግብርና ምርቶችን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ማምረት እንዳለባትም ጠቁመዋል። የቼክ ሪፐብሊክ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ሚኒስትር ቭላድሚር ባርትል በበኩላቸው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለማሳደግ በጋራ መስራት አለብን ነው ያሉት። በኢኮኖሚያዊ ትብብርና በፖለቲካዊ ውይይት በጋራ በመስራት የአገሮችን የንግድ ስርዓት ማሳለጥ ይጠበቅብናል ብለዋል። የግል ባለሃብቶች መዋዕለ-ነዋያቸውን በስራ ላይ እንዲያውሉ በማበረታታት ዘርፉን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሳደግ በቅንጅት መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። "ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት" ያሉት ምክትል ሚኒስትሩ ከምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ የንግድ መዳረሻ መሆኗን አስረድተዋል።