ቀጥታ፡

በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለሕዳሴ ግድብ ከ53 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ

ሚያዚያ 8/2013(ኢዜአ) በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ53 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችን ያቀፈ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና አማካሪ ምክር ቤትም ተመስርቷል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራ የልዑካን ቡድን በዋሽንግተንና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ትናንት ተወያይቷል።

በዚሁ ጊዜም በዲሲና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ53 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገልጿል።

አምባሳደር ብርቱካን ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ በገንዘብና በዕውቀቱ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው፤ በተለይ የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተቃረበበት ወቅት ተሳትፎውን እንዲያሳድግ  ጠይቀዋል።

ዳያስፖራው ለዘላቂ አገራዊ ጥቅሞች መረጋገጥ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ማጠናከር ይጠበቅበታል ብለዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን ለአገራቸው በተለያዩ መስኮች እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እያከናወኑት ያለውን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት የኤጀንሲውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያሳይ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል።

በውይይት መድረኩ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በሜሪላንድና ቨርጂኒያ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ያቋቋሙት የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የአማካሪ ምክር ቤት ተመስርቷል።

የተመሰረተው ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ለመስራትም ስምምነት ተፈራርሟል።

በሚኒስትር ዴኤታዋ የሚመራው የልዑካን ቡድን በቀጣይ ቀናት በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችና ከተሞች ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር እንደሚወያይ የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም